በመላ ሀገሪቱ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚወሰዱ እርምጃዎችና የተከለከሉ ጉዳዮች የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ይፋ አደረገ ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት፣ ይዘት፣ የሚወሰዱ እርምጃዎች፣ የተከለከሉ ጉዳዮችና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጌታቸው አምባዬ ይፋ አድርጓል ።
ይህንን ለማስፈፀም የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አዋጁ ተፈጻሚ የሚሆንባቸውና የማይሆንባቸውን አካባቢዎች በመለየት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ አዋጁ ተፈጻሚ እንዲሆን በተለያዩ አካባቢዎች በይፋም ሆነ በድብቅ በህዝቦች መካከል መቃቃር፣ ጥርጣሬና ግጭት የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የተከለከለ ነው።
በህዝቦችና ሃይማኖቶች መካከል ግጭትና መቃቃር የሚፈጥሩ ፅሑፎች ማዘጋጀትና ማሰራጨት፣ ትዕይንትና ምልክቶችን ማሳየትና መተግበርም አይፈቀድም ነው ያሉት።
ኮማንድ ፖስቱ የህዝብና የአገርን ሠላምና ደህንነት አደጋ ላይ ይጥላሉ ያላቸውን ማናቸውም የመገናኛ ዘዴዎች መዝጋት እንደሚችልም አስታውቀዋል ።
አዋጁ ተግባራዊ እንዲደረግባቸው በሚለዩ አካባቢዎች የመሰብሰብ፣ የመሰለፍና፣ የመደራጀት መብቶችም ሊታገዱ ይችላሉ ነው ያሉት ።
አዋጁን የሚተገብሩ አካላት በሁከትና ብጥብጥ የተጠረጠረና የተሳተፈን ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ሥር ማዋልም እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ዜጎች ተምረው ይለቀቃሉ፤ ወንጀል ፈጽመው የተገኙም በህግ አግባብ እንደሚቀጡም ገልጸዋል ።
አዋጁ ተግባራዊ በሚደረግባቸው አካባቢዎች የግለሰቦችን መኖሪያ ቤትና ተሽከርካሪ ያለፈቃድ መበርበር እንዲሁም ሰዎችን ያለምንም ፈቃድ አስቁሞ መፈተሽና መጠየቅ እንደሚፈቀድ አመልክተዋል።
በብርበራ የተያዙ ንብረቶች ወንጀል ከተፈፀመባቸውና ለመፈጸም ከታሰበባቸው ሊወረሱ ወይንም ለባለንብረቱ ሊመለሱ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩንም አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት የሰዓት እላፊ አለመታወጁን የገለፁት አቶ ጌታቸው፤ ነገር ግን ለህዝብ ይፋ በተደረጉ አካባቢዎች ሊታወጅ እንደሚችል አስታውቀዋል።
ኮማንድ ፖስቱ አደጋ የተጋረጠባቸውና አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን መንገዶችና ተቋማት ሊዘጋ ይችላል፤ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ተቋማትም ልዩ ጥበቃ ያደርጋል ነው ያሉት።
አደጋ በተጋረጠባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ሰዎችን ለተወሰነ ጊዜ በተወሰነ ቦታ የማቆየት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችልም አስገንዝበዋል።
ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቁ ለማዘዝ እንደሚችል አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል።
አዋጁ ተግባራዊ እንዲደረግባቸው በሚለዩ አካባቢዎች ዜጎች የጦር መሳሪያ፣ ተቀጣጣይ ነገርና ስለት ወይም እሳት የሚያስነሱ ነገሮች ይዞ መንቀሳቀስም የተከለከለ ነው ብለዋል።
ኮማንድ ፖስቱ የአስተዳደር እርከኖች በፈረሰባቸውና በተዳከመባቸው አካባቢዎች ከክልሉና ከህዝቡ ጋር በመተባበር የማቋቋም ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የሚከሰተውን አደጋ ጥልቀት ስፋት መሰረት በማድረግም በመደበኛ የህግ ማስከበር መከላከል የማይመለሱ ከሆነ ተመጣጣኝ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስታውቀዋል አቶ ጌታቸው።
የፍሬ ነገርና የሥነ ሥርዓት ህጎች ሊታገዱ እንደሚችሉም አክለዋል።
አዋጁ ተግባራዊ በሚደረግበት አካባቢ የሚገኙ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክበርና ለተፈጻሚነቱ የመተባበር ግዴታ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ይህን የማያከብሩና የማይተባበሩ አዋጁ በሚፈቅደው አግባብ እንደሚቀጡ አስገንዝበዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ደንብና መመሪያ ይዘጋጃል ብለዋል ።
አዋጁ በመላ ሀገሪቱ የታወጀ ቢሆንም ተግባራዊ የሚደረግባቸውን አካባቢዎች ኮማንድ ፖስቱ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ኢዜአ ዘግቧል ።