ኮማንድ ፖስቱ የሀገሪቱን ስላምና መረጋጋት በአጭር ጊዜ እንደሚመለስ አስታወቀ ፡፡
የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታርያት ዋና ሃላፊ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ እንዳስታወቁት ፤የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅመው ኮማድ ፖስት ትናንት ወደ ስራ ገብቷል ።
ኮማንድ ፖስቱ የሀገር መከላከያ ሃይል፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የክልል መንግስታት ልዩ ሃይሎችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል ።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ኮማንድ ፖስቱ ሰብአዊ መብትን አክብሮ፤ ከሀገሪቱ ህብቦች ጋር ተባብሮ የሀገሪቱን ስላም እና መረጋጋት በአጭር ጊዜ ለመመለስ እንደሚሰራም አስረድተዋል።
አቶ ሲራጅ ኮማንድ ፖስቱ በማዕከላዊነት የሚመራ ሆኖ ከላይ እስከ ታች ወጥ የሆነ ስራ የሚሰራበት እና ግዳጁን የሚፈፅምበት አሰራር የተዘረጋለት ስለመሆኑም አንስተዋል።
የኮማንድ ፖስቱ ዋና ተልዕኮም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በአግባቡ ማስፈፀም እና የሁከት እና የፀጥታ ሃይሎችን ማስታገስ ነው።
የተልዕኮው ዋና ግብም የሀገሪቱን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ እና የህዝቡን ሰላም መመለስ ነው ብለዋል አቶ ሲራጅ።
የተረጋጋ ሰላም እንዲኖር ከማድረግ ባሻገር ወሳኝ የሆኑ መሰረተ ልማት ተቋማትን ከአደጋ የመጠበቅ ስራ ያከናውናልም ነው ያሉት።
ሁሉም የፀጥታ ሃይሎች እና መዋቅሮች ራሳቸውን ችለው ሰላም እና መረጋጋትን እንዲያመጡ ማብቃትም ሌላው የኮማንድ ፖስቱ ግዳጅ ነው።
የኮማንድ ፖስቱ አባላት የሆኑ የፀጥታ ሃይል አመራሮች ትናንት ስልጠና ተሰጥቷቸዋል ያሉት አቶ ሲራጅ፤ ስልጠናው በአዋጁ ይዘት እና አዋጁን ማስተግበር የሚቻልበት እቅድ ላይ ያተኮረ ነበር ብለዋል።
በስልጠናው አዋጁን ህገ መንግስቱ በሚደነግገው መሰረት ሰብአዊ መብቶችን ሳይጥስ ማስከበር፣ ለሀገር ህልውና ለዜጎች ስጋት እና ሰላም ማጣት መንስኤ የሚሆኑ ድርጊቶችን መቆጣጠር በሚቻልበት እቅድ ዙሪያ መመከሩን ጠቁመዋል ።
እስከ ወረዳ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እስከ ቀበሌ የሚወርደውን የኮማንድ ፖስቱ መዋቅር በወጥነት ለመምራት እና ስራውን ለመስራት የሚያስችል እቅድም በኮማንድ ፖስቱ የስራ መጀመሪያ ቀን ተዘጋጅቷል ብለዋል ።
በህገ መንግስቱ በአስቸኳይ ጊዜ የማይጣሱ ተብለው የተቀመጡትን መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች ማክበርና አዋጁንም በተቀመጠው ልክ አክብሮ ማስፈፀም ኮማንድ ፖስቱ በስፋት መክሮ የተስማማበት ጉዳይ መሆኑን አቶ ሲራጅ አስረድተዋል።
ኮማንድ ፖስቱ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲገባ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈፀም ለመቆጣር የሚያስችል የክትትል ስርአት መዘርጋቱም አስታውቀዋል።
የቁጥጥር ስርአቱ ኮማንድ ፖስቱ የተሰጠውን ተልእኮ ያለ ምንም የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመፈፀም ያስችላል የሚል እምነት ተጥሎበታል ብለዋል ።
በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈፃሚ ኮማንድ ፖስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጡ ሰባት አባላትን በያዘ የአስቸኳይ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ ቁጥጥር ይካሄድበታል ሲሉም አመልክተዋል ።
ኮማንድ ፖስቱ ሰብአዊ መብቶችን አክብሮ ሀገሪቱን ወደ ቀደሞ ሰላም እና መረጋጋቷ ይመልሳል ያሉት የሴክሬታርያቱ ዋና ሃላፊ አቶ ሲራጅ፤ ህዝቡም ሰላም በማምጣት ሂደቱ ውስጥ የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።
መከላከያ ሚኒስትሩ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት በተለየ ገደብ የሚጣልባቸው አካባቢዎችም የአዋጁ ማስፈፀሚያ ደንብ እና መመሪያ መውጣት በኋላ ለህዝቡ ይፋ ይሆናል ብለዋል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።