በምዕራብ አርሲ ዞን ባለፈው ሳምንት በተቀሰቀሰው ሁከት እና ረብሻ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት መውደሙን የዞኑ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ገለፀ።
በዞኑ በሁከት እና ግርግሩ የተፈናቀሉ 1 ሺህ 800 የሚጠጉ ዜጎችም ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።
የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ፈይሳ እንደተናገሩት፥ በህዝብና የፀጥታ ሀይሎች ትብብር በሁከቱ ላይ ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች እየተያዙ ነው።
ባለፈው ሳምንት ተፈጥሮ በነበረው ሁከት በአርሲ ነገሌ የሚገኘው የአሊወዬ የውሃ ፕሮጀክት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረቱ ወድሞበታል ነው ያሉት አስተዳዳሪው።
በሻላ ሀይቅ ላይ 40 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ወጪ ተደርጎበት የተገነባውና ገና ያልተመረቀው ሎጅ እንዲሁም በላንጋኖ ሀይቅ ላይ የተገነቡት የቢሻንጋሪ እና ሲምቦ ሎጆችም ከፍተኛ የንብረት ውድመት ደርሶባቸዋል ብለዋል።
በሁከቱ ለ13 ሺ ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ እድል የፈጠሩ ሰባት የእንጨት ስራ ኢንዱስትሪዎችም ወድመዋል።
በጥፋት ሀይሎቹ ጥቃት 76 የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ተቋማት፣ 87 መጋዘኖች፣ 3 መሰረታዊ ሸቀጥ አቅራቢ ሱቆች፣ 24 የጤና ኬላዎች፣ 114 የቀበሌ ፅህፈት ቤቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችንም ከጥቅም ውጭ መሆናቸውንም ነው አቶ ሁሴን የተናገሩት።
በሁከቱ ከደረሰው የንብረት ውድመት በተጨማሪ 1 ሺህ 800 የሚጠጉ ዜጎች ለ50 አመታት እና ከዚያ በላይ ከኖሩበት ቀያቸው ተፈናቅለዋል።
በሻሸመኔ ዙሪያ 1 ሺህ 200 እንዲሁም በገደብ አሳሳ ወረዳ ሻሼ ቀበሌ ይኖሩ የነበሩ 526 ተፈናቃዮች በአሁኑ ወቅት ጊዜያዊ መጠለያ ተዘጋጅቶላቸው የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የዞኑ አስተዳደር እና ቀይ መስቀል ድጋፍ እያደረጉላቸው ይገኛል።
በቀጣይም ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት መልሶ የማቋቋም ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዞኑ አስተዳዳሪ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
የፀጥታ ሀይሎች ከህዝቡ ጋር በመሆን የጥፋት ሀይሎቹን የመለየት ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙም ነው የገለጹት።(ኤፍቢሲ)