ፕሬዝዳንቱ አርበኝነት በልማት ሊገለጽ እንደሚገባ ጠቆሙ

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ 9ኛውን የሰንደቅ ዓላማ በዓልን አስመልክተው በታላቁ ቤተመንግስት በሰጡት መግለጫ አዲሱ ትውልድ አርበኝነቱን በልማት መግለጽ እንደሚገባው ጠቆሙ፡፡

“ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን ከምንም በላይ የጠለቀና የረቀቀ ትርጉም አለው፡፡ ከታሪካችን አንጻር የነጻነታችን ጉልህ አርማ ነው፤ ከብዝሃነታችን አንጻር ደግሞ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን መገለጫ ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡

በአጠቃላይ የሀገሪቱ ሕዝብ ዘመን ተሸጋሪ ሰላም፣ የብሄራዊ እኩልነት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ጥረትና ትጋት፣ የስልጣኔ ማማ ላይ ለመውጣት የምታደርገው ትግልና የውጤቱም አርማ ነው ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ የዚህ ዘመን ትውልድ ሰንደቅ ዓላማውን በፅኑ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት መሰረት ላይ እንዲቆም እያደረገ ያለውን ያላሰለሰ ትግል ማጠናከር ይገባዋል ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶክተር ሙላቱ ገለፃ፣ 9ኛው የሰንደቅ ዓላማ በዓል የሚከበረው ሀገሪቱ 1ኛውን የዕድገትና የትርንስፎርሜሽን ዕቅድ አጠናቃ 2ኛውን የዕድገትና የትርንስፎርሜሽን ዕቅድ የጀመረችበት፣ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጄክቶችን በፍጥነት እየተከናወኑ በሚገኙበት ወቅት ነው፡፡

ከታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጄክቶች ውስጥ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ሥራ መጀመርና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ መፋጠን በሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ከማምጣት አልፈው የዜጎችን የስራ ዕድል ለማረጋገጥ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል፡፡

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ዕውቀቱን፣ ጉልበቱንና ሃብቱን በማስተባበር በሀገሪቱ የተደቀነውን የፀረ-ልማት አደጋ በተባበረ ክንድ በመመከት የሰንደቅ ዓላማውን ክብር ከፍ የማድረግ ኃላፊነትቱን እንዲወጣ ፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡