የጎንደር ከተማ ህዝብ የተጠራውን የስራ ማቆም አድማ ጥሪ አክሽፏል- የክልሉ መንግስት

የጎንደር ከተማ ህዝብ  የተጠራውን የስራ ማቆም አድማ ጥሪ ማክሸፉን የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

ከጥቅምት 7 እስከ ጥቅምት 9 ለተከታታይ 3 ቀናት የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ጥሪ የተደረገለት የጎንደር ህዝብ ይህንን የጥፋት ጥሪ በድጋሜ ባለመቀበል የተለመደውን የስራ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑንም ነው ፅህፈት ቤቱ የጠቆመው።

ትናንት የንግድና የህዝብ ተሸከርካሪዎች የተለመደውን የስራ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የዋሉ ሲሆን፥ አራዳ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ባጃጆችን ለማስቆም ጥረት ያደረጉ ግለሰቦች የነበሩ በመሆኑ ይህንን ድርጊት በማየትና በመስጋት በስፍራው የሚገኙ አንዳንድ የንግድ ተቋማት የከፈቱትን የንግድ ተቋም ለተወሰነ ጊዜ ለመዝጋት ተገደዋል።

ይሁን እንጂ እነዚህ ባጃጆችን ለማስቆም የሞከሩ ግለሰቦች በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ በስጋት የንግድ ተቋማቸውን የዘጉ ነጋዴዎች ሱቃቸውን በመክፈት ወደ ተለመደው የስራ እንቅስቃሴ መመለሳቸውንም ፅህፈት ቤቱ ከስፍራው መረጃ ደርሶኛል ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢሳትና በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ጎንደር ከተማ ውስጥ በዛሬው እለት የስራ ማቆም አድማ እንደተደረገ በማስመሰል የተሰራጩት ዜናዎች ከእውነት የራቁ መሆናቸውን ምንጮቻችን ገልፀዋል።

በቅርቡ በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት ህዝብ የሚጠቀምባቸውን ወይም ፈቃድ የወጣባቸው የንግድ ሥራዎች፣ ሱቆች ወይም የመንግሥት ተቋማት መዝጋት ወይም ምርትና አገልግሎት ማቋረጥ፣ ከሥራ መጥፋት ወይም ሥራ ማቆም እንዲሁም ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠት፣ የመንግሥት ወይም የግል ተቋማት ሰራተኞች ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዳይገቡ መዛትና ማስፈራራት የተከለከለ ስለመሆኑ እና ይህንን ፈፅመው በሚገኙ አካላት ላይ የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎች መደንገጋቸው የሚታወስ ነው- (ኤፍ.ቢ.ሲ) ።