ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጻም መርማሪ ቦርድ አባላትን ሰየመ

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ስብሳባ የሚንስትሮች ምክርቤት  መስከረም 28 2009 ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ለማስፈጸም የሚያስችሉ የመርማሪ ቦርድ አባላትን በመሰየም በሙሉ  ድምጽ  አፀደቀ።

ምክር ቤቱ የ2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ከምክር ቤት አባላትና  ከህግ ባለሙያዎች  የተውጣጡ  ሰባት  የአስቸኳይ ጊዜ  አዋጅ  አፈጻጻም  መርማሪ  ቦርድ አባላትን ለመሰየም የቀረበውን የውሳኔ  ሓሳብ  መርምሮ  በሙሉ  ጽምፅ አጽድቆታል ።

ለአዋጁ አፈጻጻም  በዋና የመርማሪ ቦርድ ሰብሳቢነት አቶ ታደሰ ሆርዶፋን፣ በምክትል ሰብሳቢነት ወይዘሮ ገነት ታደሰ የሰየመ  ሲሆን ወይዘሮ ሙና  አህመድ ፣ ወይዘሮ ኑሪያ አብዱርሃማን ፣ አቶ ክፍለ ጽዮን ማሞ ፣ አቶ ሐብቴ ፊቻላና አቶ ሰኢድ ሐሰን  የመርማሪ ቦረዱ አባላት ሆነው ተመርጠዋል ።

እንዲሁም ምክር ቤቱ  በዛሬው ዕለት  በሚንስትሮች  ምክር ቤት መስከረም  28  2009 ያወጣውን  የአስቸኳይ  ጊዜ አዋጅ ረቂቅን  የመረመረ  ሲሆን  የምክር ቤት አባላት  ላነሱት የተለያዩ  ጥያቄዎችን   ማብራሪያዎች  ከተሠጠ  በኋላ አዋጁ  በሙሉ ድምጽ  ፀድቋል ።

የአስቸኳይ  ጊዜ  አዋጁን  በተመለከተ  የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ኃላፊ  አቶ  ጌታቸው አምባዬ  ለምክር ቤቱ  በሠጡት ማብራሪያ  እንደገለጹት በአገሪቱ  የተወሰኑ አካባቢዎች የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደርናየመልማት ጥያቄዎች ሰብብ በማድረግ የተነሱ ሁከቶች    ህገመንግታዊ  ሥርዓቱን  የሚፈታተቱ ሆኖ በመገኘታቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  መታወጁን ተናግረዋል ።

መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ እንዲያደርግ ከህብረተሰቡ ከፍተኛ ግፊት  እንደነበር  የጠቆሙት  አቶ ጌታቸው የህብረሰሰቡን ሰላምና ፀጥታና እንዲሁም በልማቱ  ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመከላከል አዋጁ መውጣቱን አስረድተዋል ።

እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ ለአዋጁ ተፈጻሚነት ኃላፊነቱን የሚወጣ  በፌደራልና በክልሎች   ደረጃ  ኮማንድ ፖስት  መቋቋማቸውንና  እያንዳንዱን   እንቅስቃሴ  በአግባቡ ስለመፈጸሙ   የመርማሪ ቦርድ  አባላት  ቁጥጥር  ያካሄዳሉ ብለዋል ።