ጨፌ ኦሮሚያ የፕሬዝዳንት፣ የአፈ-ጉባኤና የካቢኔ አባላትን ሹመት አጸደቀ

ጨፌ ኦሮሚያ ለሁለት ቀናት ያካሄደው አምስተኛ የሥራ ዘመን ሁለተኛ ዓመት ሁለተኛ አስቸኳይ ስብሰባ የምክር ቤቱን አፈ ጉባኤ፣ የክልሉን ኘሬዚዳንትና የካቢኔ አባላትን ሹመት በማጽደቅ ዛሬ ተጠናቀቀ።

በዚሁ መሠረት ጨፌው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት አቶ እሸቱ ደሴን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ፣ አቶ ለማ መገርሳን ደግሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ያቀረበውን ሹመት ተቀብሎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

አቶ ለማ መገርሳ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው ከመሾማቸው በፊት የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የነበሩ ሲሆን አፈ-ጉባኤ እሸቱ ደሴም በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የፐብሊክ ሰርቪስና መልካም አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሆነው ማገልገላቸው ተመልክቷል።   

 

ተሿሚዎቹ የዳበረ የሥራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት እንዳላቸው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በከር ሻሌ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።

 

ለቀድሞው የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሙክታር ከድር ለክልሉ ልማትና ብልጽግና ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦም  ኃላፊው ምስጋና አቅርበዋል።

 

ተሿሚዎቹ ከሕዝብና ከመንግሥት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል በምክር ቤቱ አባላት ፊት ቀርበው ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።

 

ከሹመቱ በኃላ አፈ-ጉባኤ እሸቱ ደሴ ባሰሙት ንግግር "ምክር ቤቱ የሚያወጣቸው ህጎች ለህዝብ ጥቅም በአግባቡ መዋላቸውን ለማረጋገጥ አበክሮ ይሰራል" ብለዋል።

 

የምክር ቤቱ አባላት ለክልሉ ልማትና ሰላም መረጋገጥ  ያላቸውን ወሳኝ ሚና ለመወጣት ከምንጊዜውም በላይ እንዲረባረቡ ጠይቀዋል።

 

በመንግስት ጥረት ብቻ ዘላቂ ልማትና እድገትን ማረጋገጥ እንደማይቻል የገለጹት አፈጉባኤው፣  "የሕብረተሰቡን ፍላጎት በማርካት ተሳትፎውን ለማጎልበት በአዲስ የሥራ መንፈስ ጠንክረን ልንሰራ ይገባል ሲሉ" ተናግረዋል።

 

አዲሱ የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት በክልሉ በሁሉም መስክ የተመዘገቡ የልማት ውጤቶችን አጠናክረው ለማስቀጠል ሁሌም ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

 

የክልሉ መንግስት ሕብረተሰቡ በየደረጃው ለሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ለመስጠት ጠንክሮ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

 

በተለይ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት በሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ ለመተካት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ ገልጸው ለእዚህም የምክር ቤቱ አባላት ከጎናቸው እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

 

"ወጣቱ ተስፋ ቆርጦ የጥፋት ኃይሎች መሳሪያ እንዳይሆን በየደረጃው ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎውን በማጎልበት የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የክልሉ መንግስት የበለጠ ይሰራል" ብለዋል።

 

በክልሉ የተጀመሩ የሰላም፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ሁሉ የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ

 

ፕሬዝዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።

 

እንደ አቶ ለማ ገለጻ ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት ርብርብ ይደረጋል።

 

በጨፌ ኦሮሚያ አስቸኳይ ስብሰባው ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለጨፌው  አባላት ትናንት ሰፊ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

 

አፈ ጉባኤ አባዱላ እንዳሉት የጨፌው አባላት የአዋጁን አስፈላጊነት ተረድተው ወደ ተወከሉበት አካባቢ ሲመለሱ ለሕብረተሰቡ የማስረዳት ለውጤታማነቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

 

ጨፌው በፕሬዝዳንቱ የቀረቡ የ17 ካቢኔዎች፣ የክልሉን ፕሬዝዳንት ፣የክልሉን ኦዲት ቢሮ፣ የኦሮሚያ ሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽነር እንዲሁም የኦሮሚያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሹመት አጽድቋል።

 

በእዚህ መሰረት የካቢኔ አባል በመሆን የተሾሙት

 

1/ አቶ ኡመር ሁሴን – የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንትና  የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ

 

2/ አቶ ስለሺ ጌታሁን – በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት  ቢሮ ኃላፊ

 

3/ አቶ አብይ አህመድ – በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ

 

4/ ዶክተር ደረጀ ጉተማ – የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ

 

5/ አቶ ቶሎሳ ደገፋ – የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊ

 

6/ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ – የፍትህ ቢሮ ኃላፊ

 

7/ ዶክተር ሃሰን ዩሱፍ – የአካባቢ ጥበቃ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ

 

8/ ዶክተር ተሾመ አዱኛ- የዕቅድና የኢኮኖሚ ልማት ኮሚሽነር

 

9/ አቶ ሃብታሙ ኃይለሚካኤል- የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ

 

10/ ኢንጅነር ብቃሉ ሁንዴ – የኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ

 

11/ ረዳት ኮሚሽነር ደምመላሽ ገብረሚካኤል- የፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ

 

12/ ወይዘሮ ሎሚ በዶ – የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ

 

13/ አቶ አሰፋ ኩምሳ – የውሃ ማእድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ

 

14/ ወይዘሮ አዚዛ አብዲ- የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ

 

15/ አቶ ወንድማገኝ ነገራ- የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ

 

16/ አቶ ካሣዬ አብዲሳ – የቴክኒክና ሙያ ቢሮ ኃላፊ

 

17/ አቶ ብርሃኑ ፈይሳ – የኘሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ

 

ከካቢኔ አባላት ውጭ የተሾሙ

 

1/ አቶ ኤሌማ ቃጴ – የኦዲት ቢሮ ኃላፊ

 

2/ ወይዘሮ ሂሩት ብራሳ – የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር

 

3/ አቶ ጌቱ ወየሳ – የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዢን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

 

በአዳማ ገልማ አባገዳ አዳራሽ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤው ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተገኝተዋል ።

 

 

Source (ENA)