ኢህአዴግ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

ኢህአዴግ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ በውጤታማነት እንደቀጠለ የግንባሩ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በግምገማ አረጋገጠ፡፡

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከጥቅምት 14-17/2009 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባውን ማካሄዱን የድርጅቱ ጽሕፈትቤት ትናንት በወጣው መግለጫ አስታወቀ ፡፡

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች የቀረቡለትን በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ አፈፃፀም ሪፖርቶች በዝርዝር ተመልክቶ ሂደቱ በተቀመጠለት አቅጣጫ እየተጓዘ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡

ኢህአዴግና አባል ብሄራዊ ድርጅቶች የህዝባችን መሰረታዊ ጥያቄ የሆኑትን ልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላም ለማረጋገጥ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል ነው ያለው ፡፡

በአገራችን የዘለቀው ፈጣን እድገት ቀደም ሲል ለዘመናት የተጓዝንበትን የማሽቆልቆል ጉዞ በአስተማማኝ ደረጃ ቀልብሶ ወደፊት እንዲራመድ ማስቻሉን ጠቅሷል፡፡

በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ያደረገ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም መገንባት መጀመሩንም በመጠቆም ፡፡

የአገራችን ህዝቦች ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ባደረጉት ከፍተኛ  ትግል የተመዘገበው ውጤት ህብረተሰቡን ከመቼውም ጊዜ የተሻለ የመልማትና የማደግ እድል እንዲጎናፀፍ ማስቻሉን አስረድቷል ፡፡

በሌላ በኩል ድርጅቱ በአመራር የአሰራር ጉድለቶች ምክንያት የታዩ ችግሮች ስርዓቱ ለአደጋ መጋለጥ ጀምሮ እንደነበርም በግምገማው አረጋግጧል፡፡

በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴውን ወቅታዊና መሰረታዊ ሆኖ የተከሰተበት አይነተኛ ምክንያትም ይኽው እንደነበር ነው ያመለከተው ፡፡

ድርጅቱ በሂደቱ የታዩበትን ጉድለቶችም ምንጫቸው የህብረተሰባዊ ለውጥ ማምጫ መሳሪያ ሆኖ የሚያገለግለው የመንግስት ስልጣን ወደ ግል ኑሮ ማሻሻያነት ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ እንደሆነ በየብሄራዊ ድርጅቶቹ በተደረጉ ግምገማዎች በድጋሚ አረጋግጧል፡፡

ከኢህአዴግና ከብሄራዊ ድርጅቶቻችን ከፍተኛ አመራሮች ጉድለቶች ግምገማ በመጀመር የወሰነው እንደገና በጥልቀት የመታደስ አቅጣጫ በሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል ፡፡

ከመጣው ለውጥ በበቂ ሁኔታ ያልተጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም የወጣቱ የፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ጉድለት እንዲስተካከልላቸው የሚሹና የሚጠይቁ መሆኑን በአፅንኦት በመገንዘብ በአጥጋቢ ሁኔታ ለመመለስ መስራት እንዳለበት ጠቁሟል ፡፡

ድርጅቱ በጥልቀት ለማደስ የሚካሄደው እንቅስቃሴ ተፈላጊውን ውጤት እንዲያመጣም መላ የአገራችን ህዝቦች የተለመደ ገንቢ ሚናቸውን በመጫወት የለውጡን ሂደት የማይቀለበስ ደረጃ ላይ እንዲያደርሱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡