ርእሰ መስተዳድሩ በትግራይ 11 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ መታቀዱን አስታወቁ

በትግራይ ክልል በአማካይ 11 ነጥብ 5 በመቶ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማስመዝገብ መታቀዱን የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር አስታወቁ ፡፡

በክልሉ ላለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው አምስተኛው መደበኛ ጉባኤ ትናንት ሲጠናቀቅ ርዕሰ መስተዳሩ አቶ አባይ ወልዱ እንደገለጹት፤ በገጠርና በከተሞች መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ልዩ ትኩረት ተሰጥተዋል ፡፡

ለዚሁም በ2009 በጀት ዓመት የተያዘው ሁለገብ ዕቅድ የክልሉን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር መደላድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

በከተሞች እየታየ ያለው ስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ለማቃለልና ከተሞች የንግድና የኢንቨስትመንት ማዕከሎች እንዲሆኑ ይደረጋልም ነው ያሉት ፡፡

እንደዚሁም ለአነስተኛና ጥቃቅን ተቋሞች እና ማኑፋልቸሪንግ ለማጠናከር ልዩ ትኩረት እንደሚሰጣቸውም ጠቁመዋል ፡፡

በከተሞች የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግም ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ይበልጥ እንደሚበረታቱ አስታውቀዋል ፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ የውጭ ባለሃብቶችንም ለመሳብ አቅጣጫ መቀመጡን አመልክተዋል ፡፡

ስለሆነም በዚሁ በጀት ዓመት በክልሉ 11 ነጥብ 5 በመቶ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማስመዝገብ እንቅስቃሴው ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የገለጹት ፡፡

ምክርቤቱ ልዩ ልዩ አዋጆችን ጨምሮ ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ 1 ነጥብ 49 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት በማጽደቅ ማጠናቀቁን ድምጺ ወያነ ትግራይ ዘግቧል ፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግር ለማቃለል  ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮችን የመገምገም እና የማጥራት ስራ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል ።