በታንዛንያ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ለማስፈታት ጥረት እየተደረገ ነው

በታንዛንያ የታሰሩ 500 ን ለማስፈታት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከታንዛንያ መንግስትና ዓለም ዓቀፍ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር ስደተኞቹን እስከ መጪው ሕዳር ወር ድረስ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ስደተኞቹን ለማስፈታት ልዑካን ቡድን ከሳምንት በፊት ተልኮ ሂደቱን እያቀላጠፈ እንደሆነም አስታውቋል፡፡

ስደተኞቹ የታንዛንያን ድንበር ሲያቋርጡ ከወር በፊት በድንበር ጠባቂዎች እንደተያዙ አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል በዱባይ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሳ የነበረችን ኢትዮጵያዊት ለማስፈታት በዱባይ ካለው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤትና የዱባይ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን 100 ሺህ ድርሃም ተውጣጥቶ በካሳ መልኩ በመክፈል ወደ ሀገሯ እንድትመለስ ማድረግ እንደተቻለ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡

አቶ ተወልደ በማብራሪያቸው ላይ ጠቅላይ ሚንስትቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ደቡብ ሱዳን ያለውን ግጭት መፍታት በሚቻልባቸው ሁኔታወች ለመምከር ወደ ጁባ እንዳመሩም እንስተዋል፡፡

የዓለም ቤተክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶክተር አንጌላ አቦውም ኢትዮጵያ በሰላምና ልማት ያከናወነቻቸው አድንቀው፤ ምክርቤቱ ኢትዮጵያ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ሰላም ለማስከበር የምታደርገውን ጥረትም ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ቱሪስቶች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመዘዋወር መብታቸውን እንዳልተነፈገና፣ ሀገሪቱ አሁን በተሻለ ሰላምና መረጋጋት እንደምምትገኝ ገልጸዋል፡፡

ባሳለፍነው በጀት ዓመት 1 ሚሊየን ቱሪስቶች ኢትዮጵያን እንደጎበኙ አቶ ተወልደ ማስታወሳቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡

ትርጉም በሰለሞን ዓይንሸት