“በሱማሊያ ከአሚሶም የወጣ አንድም የኢትዮጵያ ሰራዊት የለም ” -መከላከያ ሚኒስቴር

“የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሶማሊያ የወጣው በሻዕቢያ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ነው የሚለው ጥርጣሬ ትክክለኛ አይደለም፤ ”  ሲሉ የሀገር መከላከያ ሚኒስትር አስታወቁ ፡፡

መከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ፤ በህብረት አፍሪካ ወይም በአሚሶም ስር ሱማሊያ ውስጥ እየተሳተፈ ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል እስካሁን በስፍራው  ነው ያለው ፡፡

“አንድም ሰራዊት ከሱማሊያ የወጣ የለም፤” ያሉት ሚኒስትሩ ፤በሱማሊያና በኢትዮጵያ ድንበር   ድንበር ላይ ያለው ውስን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኃይል ግን የአገራችንን ድንበር የሚጠብቅ በአሚሶም ውስጥ ያልተካተተ እንደ ሁኔታው የሚንቀሳቀስ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

ይህ የመከላከያ ሰራዊት እንደ አስፈላጊነቱ እና እንደ ጸረ ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴ ወደ ሱማሊያም እየገባ ወደ ኢትዮጵያም እየተመለሰ የሚሰራ ሃይል መሆኑን ነው ያብራሩት ፡፡

ጥቂት የመከላከያ ሰራዊት ኃይሎች አሁን ከተፈጠረው ሁኔታ አንጻር ካለው ጸረ ሰላም እንቅስቃሴ አንጻር ወደ ሀገሩ ውስጥ ገብቶ ያሉትን ሁኔታዎች ማየት፣ መቃኘትና ማስተካከል ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ ስለነበረ በመደበኛ ስራ እንዲንቀሳቀስ መደረጉን አስረድተዋል ፡፡

ይህ ከአልሸባብ መጠናከር ጋር ከኤርትራ ከማጥቃትም ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም ሲሉ አስገንዝበዋል የመከላከያ ሚኒስትሩ  ፡፡

በሌላም በኩል አቶ ሲራጅ የኤርትራን መንግስት በመቃወም በየቀኑ ከ40 እስከ 50 የኤርትራ ሰራዊትና ከዚህ ቁጥር የማይተናነሱ ሰላማዊ የኤርትራ ዜጎች በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ኢትዮጵያ እየጎረፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደዚሁም ስርዓቱን የጠሉ በርካታ ኤርትራውያን ደግሞ ወደ ሱዳን ፣ሳውዲና ሌሎችም አገሮች እየተሰደዱ መሆናቸውን መጠቆማቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ፡፡