ሚኒስትሩ ማህበራዊ ሚድያው ለህዝብ ጥቅም ሲባል መዘጋቱን አስገነዘቡ

ማህበራዊ ሚድያው ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ጥቅም ሲባል መዘጋቱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሰራዊት ሚኒስትሩ አስገነዘቡ፡፡

 ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ፤ማህበራዊ ሚድያው የዕውቀት መገኛ መሳሪያ ቢሆንም በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ ለብጥብጥና ለሁከት የተጠቀሙበት አካላት መኖራቸውን አመልክተዋል ፡፡

ማህበራዊ ሚድያው ብዙ የውሸት ወሬዎችን በመልቀቅ ህዝብን ክህዝብ የሚያጋጩ፣ ጥርጣሬን የሚነዙ፣ ዘረኝነትን የሚቀሰቅሱ እና የሌሉ ነገሮችን በማቅረብ ህዝብን ለረብሻ ሲሰራበት እንደነበር አስረድተዋል ፡፡

ስለዚህ ማህበራዊ ሚድያ መጀመሪያ እንዲሰራበት ከታሰበው ዓላማ ውጭ እንዲውልና የህዝቦች ሰላም እንዲረበሽ፣ ልማት እንዲወድምና የንጹሃን ዜጎች ህይወት እንዲጠፋ ምክንያት እየሆነ ነው ያሉት ፡፡

ስለዚህ ሚድያው በርካታ የአገራችን ህዝቦች ልጆቻቸው ለአላስፈላጊ ብጥብጥ እና በማያውቁት ቀውስ ውስጥ እንዲገቡባቸው እያደረገባቸው በመሆኑ እንዲቆምላቸው መጠየቃቸውንም አንስተዋል ፡፡

ስለሆነም በሀገሪቱ የሰው ህይወት ከመጥፋቱም በላይ ልማት እየቆመ፤ በህዝቦች መካከል ጥርጣሬ እየተፈጠረ ነው የሚል የህብረተሰቡ ጥያቄ አግባብነት ያለው መሆኑን መንግስት መገነዘቡንም ጨምረው ገልጸዋል ፡፡

እንደዚህ ዓይነት ቅስቀሳና ችግር የሚፈጥሩ የመገናኛ ዘዴዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመሪያ አፈጻጸም ወይም ደንቡ ይከለክላቸዋል ነው ያሉት ፡፡

ይህ የመከልከሉ ሁኔታ በሂደት እንዴት ይፈታል? የሚለው አሁን እየተፈጠረ ያለው መረጋጋት እየተጠናከረ በሚሄድበት ሰዓት ሁኔታው ታይቶ ተገምግሞ ሊከፈት የሚችልበት ሁኔታ እንደሚኖር አስታውቀዋል ፡፡

አፍራሽ ድርጊት የሚፈጸምበት ሆኖ ከተገኘ ደግሞ ለህዝብ ሰላምና ጥቅም ሲባል ሊታገድ የሚችልበት ሁኔታ ዝግ አለመሆኑን ነው ያስገነዘቡት  ፡፡

ከዚያ ውጭ ያሉት የኢንተርኔት አግባቦች ግን ከዚህ ብጥብጥና ሁከት ነጻ በሆነ መልኩ በአዲስና የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም እየሰፉ በመሄዱበት መንገድ መንግስት በራሱ ጊዜ ምላሽ የሚሰጥበት መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡

ሚኒስትሩ “ማህበራዊ ሚድያው በአግባቡ ከተጠቀሙበት ኢንፎርሜሽን የሚለዋወጡበትና ዕውቀት የሚገበያዩበት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይታወቃል፤ ብዙ አገሮችም ላይ በዚሁ ይሰሩበታል ብየ አምናለሁ፤” ማለታቸውን የዋልታ  ዘገባ አመልክቷል ፡፡