መንግስት ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ማካሄድ እንዳለበት ምክር ቤቱ ጠየቀ

መንግስት እስከታች ባሉ መዋቅሮች የህዝብ መብት የሚከበርበትን አግባብ መፍጠር እንዳለበትና ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋርም ውይይት እና ድርድር ማካሄድ እንዳለበት የሃገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ፓርቲዎች ጠየቁ፡፡

ምክር ቤቱ በመደበኛው ስብሰባው በወቅታዊ የሃገሪቱ ሁኔታ ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በጋራ ምክር ቤቱ የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ኢሕአዴግ እንደ ገዢ ፓርቲና እንደ መንግሥት እያከናወኗቸው ባሉ ሥራዎች ዙሪያ ማብራሪያ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ፓርቲዎቹ በዚሁ ጊዜ መንግሥት በፌዴራል ደረጃ የሚያከናውናቸው ለውጦች በአዎንታ የገለጹት ሲሆን ለውጠቹ ውጤታማ እንዲሆኑ እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን መውረድ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

የቅንጀት ለአንድነት ለዴሞክራሲ ፓርቲ ተወካይ አቶ ደሳለኝ በሻ እንደተናገሩት ድርጅቱ ለተፈጠሩት ችግሮች በጎ መፍትሄዎችን አስቀምጧል።

በመፍትሄዎቹ ዙሪያ ታች ወርዶ ከህዝቡ ጋር በመወያየት ለውጥ ማምጣት ይጠበቅብታል ነው ያሉት።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ተወካይ አቶ አለማየሁ ዘለቀ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ገዢው ፓርቲ የጀመረው በጥልቀት የመታደስ ሥራ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በተገባው ቃል መሰረት ራሱን የማደስ እንቅስቃሴው በተግባር መጀመሩ የሚበረታታ ነው ብለውታል።

ድርጅቱ ሁሉንም የአስተዳደር እርከኖች እየፈተሸ እስከ ታች ድረስ ለውጥ መድረስ ካልቻለ ውጤታማ አይሆንም የሚል ስጋት እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ እንቅስቃሴ (የመኢብን) ኃላፊ አቶ መሳፍንት ሽፈራው ናቸው።

በውይይቱ ላይ የኢህአዴግ ተወካይ አቶ ረዳኢ ሓለፎም እንዳብራሩት የህዝቡ የመልማት ፍላጎት ከፍተኛ መሆንና የመንግሥት አቅም ማነስ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር መንሰራፋቱ ለተፈጠሩት ችግሮች ምክንያት ሆነዋል።

ሕዝቡን በአግባቡ የማሳተፍ ችግር፣ ሕዝቡ እኩል ተጠቃሚ ያለመሆንና የመሰረተ ልማት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት ሌላው እንደሆነም በመጥቀስ።

ከዚህ ባለፈ የወጣቱ የሥራ አጥነት መጨመር፣ በውስጥም በውጭም ያሉ ጠላቶች ተባብረው የሕዝቡን ጥያቄ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መውሰድ እንዲሁም በሕዝቦች መካከል ልዩነት የመፍጠር እንቅስቃሴዎች መደረጋቸው ደግሞ አባባሽ ምክንያቶች ነበሩ ብለዋል አቶ ረዳኢ።

ለእነዚህ ችግሮች እንደ መንግሥትና ገዢ ፓርቲ ራሱን በጥልቀት እያደሰ መሆኑን አውስተው በየደረጃው ውይይቶች በማካሄድ መሰረታዊ ለውጦች እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።

ለውጡም ከላይ ጀምሮ እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት እየተከናወኑ መሆኑናቸውን አስረድተዋል።( ኢቢኮ)