አርበኞች ግንባር የፖለቲካ ልዩነቱን ጠብቆ ለአገር ብልጽግና እንደሚሰራ አስታወቀ

የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር የፖለቲካ ልዩነቱን ጠብቆ በሰላማዊ መንገድ  ለአገር  ብልጽግና እንደሚሰራ አስታወቀ ፡፡

የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ትዋት ፓል ቻይ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ከዚህ በፊት በተካሄዱ ተደጋጋሚ ጥረቶች ከትጥቅ ትግል ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመሸጋገር የሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሰዋል ፡፡

ሊቀመንበሩ በደቡብ ሱዳን ላለፉት ሰባት ዓመታት ከኢትዮጵያ መንግስት የተጀመረ የሰላም ድርድር በተለያዩ ጊዚያቶች በተለያዩ ምክንያቶች እየከሸፈ ቆይቷል ነው ያሉት ፡፡

ይህም በግንባሩና በመንግስት መካከል የነበሩ አንዳንድ አደራዳሪዎች የኢትዮጵያ ሉአላዊነት፣ አንድነት፣ ሰላምና ፍትሕ እንዲሰፍን ፍላጎት ስላልነበራቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አደራዳሪዎቹ ሰዎች ነገሮችን የሚያዩት ከራሳቸው አንጻር ስለሆነ ለኢትዮጵያውያን ሰላም የሚደረጉ ጥረቶች የመሰላቸት ሁኔታዎች ስለሚያሳዩ እንደነበረም አመልክተዋል ፡፡

አንዳንዶቹ ደግሞ የራሳቸው ድብቅ አጀንዳ ስለነበራቸው በዚህም የተነሳ ይህንን ለመሸምገል ባገኟቸው አጋጠሚዎች ተገቢውን የወዳጅነት ስራ ባለመስራታቸው መሆኑን ነው ያስረዱት ፡፡

አሁን ግን የኢትዮጵያ መንግስትና አርበኞች ግንባር ሰላም ለመፍጠር እየተፈላለጉ ከቆዩ በኋላ መስማማታቸው ትልቅ ድል መሆኑን አቶ ቱዋት አስገንዝበዋል፡፡

ከሁሉም በላይ መቅደም ያለበት የኢትዮጵያ ህልውና ነው ያሉት ሊቀመንበሩ ፤ስለአንድ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ማውራት የምትችለው አገር ስትኖር  ብቻ መሆኑን በመገንዘብ መስማማታቸውን አስረድተዋል ፡፡

ግንባሩ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ ያምናል ያሉት አቶ ትዋት፤ኢትዮጵያ በተሻለ ዕድገት ቀድሞ በነበረው ቅርጿ ጠብቃ ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ የውዴታ ግዴታ ያላቸው መሆኑን አስገንዝበዋል ፡፡

ግንባሩ በኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች የሚያምኑ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የተውጣጡ የቀድሞ ሰራዊት አባላት የነበሩ፣ ህዝባዊያን ድርጅቶች አባላት የነበሩና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ያካተተ እንደሆነም ገልጸዋል ፡፡

የድርጅቱ ሰላም አደራዳሪና የደህንነት ኃላፊ ጌታነህ ዘለቀ በበኩላቸው የስምምነቱ መነሻ ቀደም ብለው ውጭ ሆነው በተለያየ ጊዜ የተለያዩ የመግባቢያ ሰነዶች የተፈራረሙትን ወደ ተግባር ለመለወጥ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡

ስምምነቱን በመንተራስም የታቀዱ ቅድመ ዝግጅቶች ስላሉ የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ትግባራዊ ስራ እንደሚገቡም ነው የገለጹት ፡፡

ሰላም ከሌለ አገር ብሎ ነገር የለም ያሉት አቶ ጌታነህ ፤ግንባሩ ይህንን በማወቅ ለሰላም ቅድሚያ መስጠቱን አስገንዝበዋል ፡፡

ድርጅቱ በረሃም ሆኖ ስለአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ቆም ብሎ በማሰብ የኢትዮጵያ ህዝብ ጽኑ ፍላጎት ሰላም መሆኑን በማየት የታጠቁትን መሳሪያ ለማስቀመጥ መወሰናቸውን አስረድተዋል ፡፡

የግንባሩ ሰራዊት ተወካይና የሰላም አደራዳሪ ቡድን አባል አቶ ባንጋቦል ኡማን ደግሞ ሰራዊቱ ከ2004 ዓመተ ምህረት አንስቶ ማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ በየቦታው አርፎ እንዲቀመጥ ትእዛዝ መሰጠቱን አስታውቀዋል ፡፡

የግንባሩ ሰራዊት አባላት በሰሜን ሱዳን ፣በኡጋንዳና በኬንያ ተቀምጠው ይገኛሉ ያሉት አቶ ባንጋቦል ፤ሰራዊቱ፣ የጎሳ መሪዎችና ደጋፊዎች ድርጅቱ በሰላማዊ መንገድ የመታገል  አቋም እንዲደግፉ ማድረጋቸውን ገልጸዋል ፡፡

ስለሆነም “ባሁኑ ሰዓት የሰራዊቱ አባላት ወደ አገርቤት ለመግባት ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት  የተነሳ ስምምነቱን ጨርሰን በሰላም መመለስ በጉጉት እየጠበቁ ናቸው ” ነው ያሉት ፡፡

ስለሆነም ሁለቱም ወገኖች ስምምነቱን መፈረም ተከትሎ ቀሪ ስራዎች ከጨረሱ በኃላ በመንግስት በጎ ፈቃደኝነት እንደሚመለሱ አስታውቀዋል ፡፡

በቅርቡም ይህንን የምሰራች በጎሮቤት አገሮች ለሚገኙ ሰላም ፈላጊ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለመግለጽ እንደሚሰማሩም አቶ ባንጋቦል አስታውቀዋል ፡፡

ሌሎች መሳሪያ ያነሱ ወገኖች ሁሉ ለሀገራቸው ህዝብ ሰላምና ብልጽግና ልዩ ትኩረት በመስጠት ፖለቲካዊ ዓላማቸውን በሰላም ማራመድ እንደሚችሉ በመገንዘብ ወደ ህዝባቸው እንዲቀላቀሉ የግንባሩ አመራሮቹ ጥሪ አስተላልፈዋል ፡፡