ለበዓሉ ወደ ሐረር ለሚጓዙ እንግዶች ሆቴልና ማረፊያ ቦታዎች ተዘጋጁ

ህዳር 29 ቀን በሀረር ከተማ ለ11ኛ ጊዜ ለሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ለእንግዶች ሆቴልና ማረፊያ ቤቶች መዘጋጀታቸውን የሐረሪ ክልል አስታወቀ፡፡

በዓሉን ለማክበር ወደ ክልሉ ለሚመጡ እንግዶች ጥራታቸውን በጠበቁ ሆቴሎች 500 ማደሪያዎች መለየታቸውን የበዓሉ የሎጀስቲክስና እንግዳ አቀባበል ንኡስ ኮሚቴ ገልጿል፡፡

እነዚህም ለከፍተኛ እንግዶች የተዘጋጁ ማረፊያዎችና ማደሪያዎች መሆናቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ኮሚቴውን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡፡፡

የሆቴሎችን ደረጃ ከፍ ከማድረግ በተጓዳኝ ሆቴሎች አስፈላጊዎቹን ግብዓቶች አሟልተው እንዲገኙ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ኮሚቴው አስረድቷል፡፡

እንግዶችን በደንብ ለማስተናገድ 200 ለሚሆኑ የሆቴል ባለሞያዎችና 25 በቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት በመስተንግዶ እና ጉብኝት ዙሪያ ለ10 ተከታታይ ቀናት በሙያ ስነ ምግባርና ክህሎት ማጠናከሪያ ዙሪያ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ወክለው ለሚመጡ ልዑካን ማረፊያ እየተዘጋጀ መሆኑን ኮሚቴው አስታውሶ ግንባታው ቶሎ እንዲጠናቀቅም ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብሏል፡፡

ለእንግዶች እየተዘጋጁ ያሉት ማረፊያ ቤቶችም እስከ ህዳር ወር 2009 ዓ.ም የመጀመሪያ ሳምንት ጊዜ እንዲጠናቀቁ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሐምዛ መሀመድ ማስገንዘባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአቶ ሐምዛ የሚመራው የክልሉ ከፍተኛ አመራር የቀላዳንባ፣ የሐማሬሳ፣ የቱርክ ትምህርት ቤት እና የሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የእንግዶች ማረፊያ ቤቶችን ጎብኝቷል፡፡ የቤቶቹ ግንባታ በታቀደላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የቀላዳንባ እንግዶች ማረፊያ የመፀዳጃ፣ የመታጠቢያ፣ የመመገቢያ ግብዓቶች፣ የመብራትና የውሃ አቅርቦት እንዲሁም ግቢውን የማስፅዳት ሥራ ፅዳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለእንግዶቹ ምቹ  እንዲሆን መመሪያ ተላልፏል፡፡

በሐማሬሳ የሚገኘው የጥቃቅንና አነስተኛ እንግዶች ማረፊያ የማጠቃለያ ስራ እንዲፋጠንም ከፍተኛ አመራሮቹ አሳስበዋል፡፡ ለዚህ የሚያፈልገውን ድጋፍ የክልሉ መንግስት እንደሚያደርግ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል፡፡

በበዓሉ ላይ ከ3000 በላይ እንግዶች ይታደማሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ለእነዚህም ከሆቴሎች በተጨማሪ ከስምንት በላይ የእንግዶች ማረፊያ ቤቶች መዘጋጀታቸውን ክልሉ አመልክቷል፡፡