ፍርድ ቤቱ የተገልጋይ እርካታን የሚያረጋግጡ አሰራሮችን እየተገበረ ነው

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገልጋይ እርካታን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አሰራሮችን እየተገበረ መሆኑን ገለፀ፡፡  

ፍርድ ቤቱ በባለሙያዎች የተገልጋይ እርካታ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ የተገኙ ክፍተቶችና ጉድለቶችን በመለየት የተሻለ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት እየሰራ መሆኑን የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት የኔነህ ስመኝ ለዋልታ ገለፁ፡፡

በጥናቱ ተገልጋዮች አሉ የሚሏቸውን ችግሮች ማስቀመጣቸውን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመው በዚህ ዙሪያም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየትና በመመካከር የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ነው፡፡

የቀጠሮ ፖሊሲን ጠብቆ ያለመስራት አንዱ ችግር ሲሆን በዚህም ለፍርድ፣ምስክር ለመስማት፣ ለክርክር፣አጭርና ረጅም ጊዜ የሚወስዱ ጉዳዮችን በተመሳሳይ ሠዓት በመቅጠር ባለጉዳዮችን የማጉላላት አካሂድ በስፋት እንደሚስተዋል በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

የተዘዋዋሪና የፕላዝማ ችሎቶች በሙሉ አቅም አለመስራት፣ የቀጠሮ መርዘም፤አድሎአዊ አሰራርና ሙስና፣ ጠንካራ የመረጃ ማዕከል አለማደራጀት፣ ጠንካራ የፍርድ ቤት ውሳኔ አፈፃፀም አለመኖር፤ የፍርድ ቤቶችን አሰራር ለህብረተሰቡ በደንብ አለማሳወቅን የመሳሰሉ ችግሮች መኖራቸውም ተመልክቷል፡፡

በጥናቱ የተለዩት ግኝቶች መኖራቸውን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ ሁሉም ፍርድ ቤቶች የቀጠሮ ፖሊሲን መሰረት ያደረገ፣ እንደ ጉዳዮቹ ባህርይ ተገልጋዮችን በተለያየ ሠዓት በመቅጠር እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ሁሉም ተዘዋዋሪ ችሎቶች በሙሉ አቅም እንዲሰሩ፣አጭር ቀጠሮ በመስጠት ፍትሃዊ ሂደትን የተከተለ አሰራርን እንዲተገብሩ ይደረጋል፡፡ የፍርድ ውሳኔዎችም በፍጥነት እንዲፈፀሙ፣የመረጃ ማዕከልን በሰው ኃይልና በግብዓት የማደራጀት ሥራ እንደሚሰራም ነው የገለፁት፡፡

በመብራት፣በኔትወርክና በቀላሉ ሊጠገኑ በሚችሉ የቴክኒክ ችግሮች ምክንያት የሚፈለገውን አገልግሎት መስጠት ያቆሙት የፕላዝማ ችሎቶች በሙሉ አቅም እንዲሰሩ የጀኔሬተር ግዥና የኔትወርክ መቆራረጥን ለማስቀረት ከሚመለከተው አካል ጋር ምክክር ተደርጓል ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በክልል ደረጃ ስልሳ የፕላዝማ ችሎቶች አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም አሁን በትክክል አገልግሎት የሚሰጡት 15 የፕላዝማ ችሎቶች ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል፡፡ እነዚህ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡

አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ፍርድ ቤቶች ራሳቸውን በማሻሻል በጥናቱ ለተለዩት ድክመቶችና ጉድለቶች ዘላቂና አፋጣኝ መፍትሔ ይሰጣል፡፡

ዳኞችና ሠራተኞች በህዝብ አገልጋይነት ስሜት እንዲሰሩ ማድረግ፣ አቤቱታ የሚቀርብበት ፎርም በማዘጋጀትና አገልግሎት አሰጣጡም በዜጎች ቻርተር መሰረት ይተገበራል፡፡ ይህን ጉዳይ የሚከታተል ፅህፈት ቤትም ይቋቋማል፡፡