ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት መትጋቷን ቀጥላለች

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን እያከናወነችው ያለው ጥረት አስጠብቃ መቀጠሏን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ጨምሮ ኢትዮጵያ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ከኢጋድ፣ አፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመሆን ጉልህ ሚና እንዳላት ተገልጿል፡፡

የሚኒስትሩ ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት ፤ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር የውጭ አገራት ጋር ባላት የትብብር ፖሊሲ በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ውጤታማ ሥራዎችን አከናውናለች ፡፡

ኢትዮጵያ ከሱዳን፣ ኬንያ፣ ጅቡቲና ደቡብ ሱዳን በርካታ የትብብር ስምምነቶችን እደተፈራረመችና ይህም በፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ከእነዚህ ሀገራት ጋር ያለውን ወንድማማችነትና ትብብር ወደተሻለ ከፍታ ላይ ማድረስ እንደተቻለ ነው የገለጹት ፡፡

በአሚሶምና የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች በሶማሊያና ሱዳን የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን በመላክ አትዮጵያ ለሰላም ያላትን ቁርጠኛ አቋም በተግባር እንዳሳየች አቶ ተወልደ አክለው ገልጸዋል፡፡

ሰላም ከማስከበር ባሻገር ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን እስከ 10ሺህ የሚደርሱ የሱዳን ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናደች እንደሆነም አስታውቀዋል ፡፡፡

የደቡብ ሱዳን መሪዎችን በማግባባት የስምምነት ፊርማ እንዲያኖሩና ለተግባራዊነቱ እንዲተጉ የሚደረገውን ጥረት ተጠናክሮ እደሚቀጥልም ነው ያመለከቱት ፡፡

በቀጠናው ያለውን ውስን የኢኮኖሚ ትስስር በማጎልበት አገራቱ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ተግባራትም እየተከናወኑ መሆኑ ይታወቃል ፡፡