በሐረሪ ክልል ለ11ኛ ጊዜ ለሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ዝግጅትን ተከትሎ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ ፡፡
ለበዓሉ ወደ ክልሉ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በሚደረገው ዝግጅት የክልሉን ዕድገት የሚያፋጥኑ የተለያዩ ልማቶች መከናወናቸውን በፌዴሬሽን ምክር ቤት የበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ ፀሀፊ ወይዘሮ ፍሬወይኒ ገብረ እግዚአብሔር ለዋልታ አስታውቋል፡፡
የባህል ማዕከል፣ የስታዲየም፣ የሆቴል፣ የእንግዳ ማረፊያዎችና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በስፋት መገንባታቸውን ገልፀዋል፡፡
ክልሉ በዓሉን በድምቀት ለማክበር በሚያደርገው ዝግጅት ለክልሉ ዕድገትና ገፅታ ግንባታ የሚረዱ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል ፡፡
በተለይም የባህል ማዕከልና የስታዲየሙ ግንባታዎች ከተያዘላቸው ጊዜ ቀድመው እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ፀሀፊዋ አስታውቀዋል፡፡
ይህም የክልሉ ህዝብና መንግስት እጅና ጓንት ሆነው በመስራታቸው የመጣ ውጤት መሆኑን ነው ያስረዱት ፡፡
የከተማዋን ፅዳት የማስጠበቅ ሥራዎችም በስፋት ከመከናወናቸውም በተጨማሪ ቀደም ሲል ተገንብተው የነበሩ ሆቴሎችና የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት መታደሳቸውን አብራርተዋል ፡፡
የቱሪስት ማረፊያ ሆቴሎችም ተገቢውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ኮሚቴው መገምገሙ ተመልክቷል፡፡
የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በአስፓልትና በኮብልስቶን ደረጃ በመገንባታቸው ወደ ቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች የሚወስዱ መንገዶችም ለቱሪስቶች ምቹ ሆነዋል ነው ያሉት ፡፡
ክልሉ እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ ባሉት ቀናት ለበዓሉ ድምቀትና እንግዶችን በደንብ ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚረዱ ተግባራትን የማከናወን ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠሉ ነው ያስረዱት ፡፡
ከክልሉ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየተገነባ ያለው የባህል ማዕከል ከ2 ሺ 300 በላይ ሰው ያስተናግዳል፡፡
አዲስ ከሚገነባው ከአው አባድር ስታዲየም ግንባታ በተጨማሪ የኢማም አህመድ ስታዲየም እድሳት እየተደረገለት መሆኑን ነው የተገለጸው ፡፡
ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸውን ቋንቋቸውንና ማንነታቸውን የሚያንፀባርቁበት፤ ልምድ የሚለዋወጡበት ይኸው ብሔራዊ በዓል ህዳር 29 ‹‹ህገ መንግስታችን ለዲሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለህዳሴያችን›› በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር መገለጹ ይታወሳል ፡፡