ሚኒስትሩ መረጃዎች በትክክል ለህዝብ እንዲደርሱ ልዩ ትኩረት መስጠቱን አስታወቀ ።

መረጃዎች በትክክል በማድረስ የህዝብ እና የመንግስትን ግንኙነት ይበልጥ የማጠናከር ስራ እንደሚሰራ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አስታወቁ ፡፡

ኃላፊ ሚኒስትሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንዳስገነዘቡት ፤እያንዳንዱ የህዝብ ግንኙነት ስለ መስሪያ ቤቱ በቀጥታ መረጃን እንዲሰጥ የሚደረግ ሲሆን፤ዋና ዋና ጉዳዮች ደግሞ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አማካይነት ይሰጣል ።

በመንግስት በኩል መረጃን በፍጥነት የመስጠት ችግር አለብን ያሉት ሚኒስትሩ፤ የችግሩ ምንጭ ወደ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ቶሎ መረጃን ያለማድረስ ፤የተገኘው መረጃም ቢሆን ጥራት የሌለው እና የተሸፋፈነ መሆኑን አስታውቀዋል

ለበርካታ አመታት በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ላይ ጥናት እና ምርምር ያደረጉት ዶክተር ነገሪ፤በታዳጊ ሀገራት የሚኖር ህዝብ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ድህነት ውስጥ የሚኖር ነውይላሉ።

ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድህነት እና ያልዳበረ ዴሞክራሲ ባለበት ሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የህዝቡን ነባራዊ ሁኔታን በትክክል የሚገልጽ መረጃ ሊሰጡ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት፡፡

ይሁንና ሚኒስትሩ ባካሄድኩት ጥናት ጋዜጠኛው ታች ድረስ ወርዶ የህዝቡን ጥያቄ ይዞ ሲመጣ የመንግስትን በጎ ስም ያጠፋል በሚል ምክንያት ዜናውን የሚጥሉ ሚዲያዎች እንዳሉ ገልጸዋል ።

ይህ ደግሞ ጋዜጠኛውን ከምርመራ ስራዎች ይልቅ የስኬት ዜና ለመስራት እንዲገደድ ያደርጋልሲሉም ዶክተር ነገሪ አስረድተዋል።

በዚህ ጊዜም ህዝብም ማግኘት ያለበትን መረጃዎች እንዲያጣ ይደረጋል ነው ያሉት ፡፡

ይህም በመንግስት እና በህዝብ መካከል የተፈጠረውን ክፍተት ደግሞ ጽንፈኞች በአግባቡ የቤት ስራቸውን እንዲሰሩበትና የህዝብ ድምጽ በሌላ መንገድ እንዲገለጽ እድል የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል ።

 መንግስት መረጃን የማፈን መብት የለውምያሉት ሚኒስትሩ ፤ አሁን በሀገሪቱ የሚታየው ችግር መብቱ ተሰጥቶ ሳለ በህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ዘንድ መረጃን በመደበቅ፣ አለቃን የማስደሰት ፍላጎትና የስኬት ዜናዎች ብቻ እንዲወሩ መፈለግ ናቸው የችግሮቹ ምክንያቶች” ሲሉ ያስገነዝባሉ

በቀጣይ መረጃዎች በትክልል ለህዝብ የሚደርሱበት ግልጽ የሆነ አሰራር ይዘረጋል ያሉት ዶክተር ነገሪ ፤ በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ለመገናኛ ብዙሃን አካላት ዓቅምን የመገንባት ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል ።

ትክክለኛ እና በአፋጣኝ መረጃን የማይሰጡ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር ይዘረጋልሲሉም አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ እንደሚኒስትሩ ገለጻ ከሆነ፤መንግስት በከፍተኛ አመራሩ የጀመረውን ጥልቅ ተሃድሶ እስከታችኛው አመራር ድረስ ካልቀጠለ የይስሙላ ነው የሚሆነው ።

በክልሎች ከሰሞኑ እየተደረገ ያለው የተሃድሶ ግምገማም ለውጡን እስከታች የማውረድ ሂደት አካል መሆኑን ዶክተር ነገሪ አስረድተዋል –(ኤፍ..)