ኢትዮጵያ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማራካሹ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የጎላ ሚና መጫወቷን የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አስታወቀ ።
በሞሮኮ ማራካሽ የተካሄደው ጉባኤ ዓምና ከተካሄደው የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በመቀጠል የተከናወነ ሲሆን አገራት የፓሪሱን ስምምነት እንዲፈርሙና ተግባራዊ እንዲያደርጉ ግፊት ለማሳደር ተብሎ የተዘጋጀ ነው ።
የፓሪሱ ስምምነት በዓለም ላይ የአየር ንብረትን ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል የሚያስችል ፈር ቀዳጅ ስምምነት እንደሆነ የሚነገርለት ሲሆን 170 የሚደርሱ አገራት በማራካሽ ስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል ።
የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ በትናንትናው ዕለት በሠጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በደን ልማትና በስነምህዳር ጥበቃ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወኗ ለሌሎች አገራት እንደ ምሳሌ የሚወሰድ ነው ብለዋል ።
የአገሪቷ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲም ከዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተግባራትና እርምጃዎች ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ገመዶ ኢትዮጵያ የታዳሽ የኃይል ምንጮችን በማስፋፋት በዓለም የፀረ – የአየር ንብረት ለውጥ ተከራካሪ መሆን ችላለች ብለዋል ።
ኢትዮጵያ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የሆኑ 47 አገራትን በማሰባሰብ በአየር ንብረት ላይ ከፍተኛ ብክለት የሚያደርሱ አዳጊ አገራት ለታዳጊ አገራት ካሳ እንዲከፍሉ በመከራከር ላይ መሆኗን ዶክተር ገመዶ ተናግረዋል ።
ሁሉም የፓሪሱ ስምምነት ፈራሚዎች የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ መምሪያዎችን እኤአ በ2017 በማውጣት እኤአ በ2018 መመሪያዎችን የማውጣት ሥራን ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ በእኤአ በ 2020 ስምምነቱን ተግባራዊ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ።