ኢትዮጵያ ድንበር ጥሰው የገቡ 20 ቀላል አውሮፕላኖችን በቁጥጥር ሥር አዋለች

ከሁለት ቀን በፊት 20 ቀላል የሲቪል አውሮፕላኖች ከሱዳን ተነስተው የኢትዮጵያን ድንበር ያለፍቃድ ጥሰው በመግባታቸው  በቁጥጥር ሥር  መዋላቸውን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ትናንት በሰጡት መግለጫ፥ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ተልዕኳቸው ያልታወቀና ቀድመው ወደ ኢትዮጵያ የአየር ክልል ለመገባት ፍቃድ ያልጠየቁት ቀላል አውሮፕላኖች  የኢትዮጵያን አየር ክልል የመጣሳቸው ምክንያት እየተጣራ ነው ብለዋል።

አውሮፕላኖቹ በአሁኑ ጊዜም በጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲያርፉ መደረጋቸውን ነው ባለስልጣኑ በመግለጫው ተመልክቷል።

ከትናንት  በስተያ አመሻሽ ላይ  የኢትዮጵያን የአየር ክልል ጥሰው  የገቡት አውሮፕላኖች ስንት ሰው  እንዳሳረፉ  ፣ የየት አገር ዜግነት እንዳላቸውና ንብረትነታቸው የማን እንደሆነ አውሮፕላኖቹ በቁጥጥር ሥር ውለው  ለማጣራት ከትላንት በስተያ ጀምሮ  ተጨማሪ ምርመራ ቡድን  ወደ ጋምቤላ   ተልኳል ።

እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከባለስልጣኑ መስሪያ ቤቱና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ምርመራ እየተካሄደ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም አጠቃላይ የምርመራ ውጤቱ ከተጠናቀቀ በኋላ መንግሰት ጉዳዩን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ መግለፃቸውን ባለስልጣኑ ያደረሰን መግለጫ ያመለክታል።

በዓለም አቀፉ  የበረራ ህግ መሠረት ማንኛውም አውሮፕላን  የአገራትን ሉዓላዊነት  በጣሰ መንገድ በየትኛውም አገር ላይ  ማረፍ ወይም መብረር አይችልም ።