ህገ መንግስታዊ አስተምህሮን በዘላቂነትና ወጥነት ባለው መንገድ ለማስቀጠል የስትራቴጂክ ዕቅድ ማዘጋጀቱን ፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
ምክር ቤቱ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አካላትን በማቀናጀት የህብረተሰቡ ህገ መንግስታዊ ግንዛቤ ያለበትን ደረጃ ማስጠናቱን በምክርቤቱ የዲሞክራሲ አንድነት የህገ መንግስት አስተምህሮትና የሠላም ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ወይዘሮ ፍሬወይኒ ገብረ እግዚአብሔር ለዋልታ ገልጸዋል፡፡
በጥናቱም የህብረተሰቡና የአመራሩ ህገ መንግስታዊ ግንዛቤ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ መቻሉን ጠቁመዋል ፡፡ ፡፡
ይህን መነሻ በማድረግም ግንዛቤውን በስፋትና ባልተበጣጠሰ መንገድ ለማሳደግ የህገ መንግስት አስተምህሮት ስትራቴጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱን ነው ፀኃፊዋ የገለፁት፡፡
ስትራቴጂክ ዕቅዱ ቀደም ሲል በተበጣጠሰ መንገድ የሚሰጠውን ህገ መንግስታዊ አስተምህሮ በተቀናጀና ወጥነት ባለው መንገድ ለማስኬድ የሚያስችል አሰራር ለመዘርጋት ይረዳል ተብሏል፡፡
አስተምህሮቱን ለማስፋትና ለማጠናከር በሚደረገው ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች የሚገመገሙበትና የመፍትሔ አቅጣጫ የሚቀመጥበት አካሄድም ተግባራዊ ይሆናል፡፡
የስትራቴጂክ ዕቅዱ መጠናቀቁን ወይዘሮ ፍሬወይኒ ጠቁመው ከተለያዩ ምሁራንና የህብረተሰቡ ክፍሎች ጠቃሚ ግብዓቶች መሰብሰባቸውን አስረድተዋል፡፡
በታህሳስ ወር 2009 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ በሚዘጋጅ የማፅደቂያ ጉባዔ ላይ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከአፀደ ህፃናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ አስተምህሮቱን ከማስፋፋት በተጓዳኝ የትምህርት ሥርዓቱን የመፈተሸ ሥራም ይከናወናል፡፡ በሲቪክና በሥነ ምግባር ትምህርት ዘርፍ የሚሰጠው ህገ መንግስታዊ አስተምህሮ እንዲጠናከር እንደሚደረግም ነው ፀኃፊዋ የጠቆሙት፡፡
ምክር ቤቱ ከትምህርት ተቋማት፣ ከመከላከያ፣ ከፖሊስና ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሚሰጠውን የአሰልጣኝነት ሥልጠና ሥራ በቀጣይም ተጠናሮ እንደሚቀጥል አስገንዝቧል፡፡
የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተቋማትም በደንብ ተጠናክረው የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ይሰራል፡፡ሁሉም ህብረተሰብ በየተሰማራበት ዘርፍ ህገ መንግስታዊ ግንዛቤውን የሚያሳድግበት መንገድ ይመቻቻል፡፡