ኮሚሽኑ የድርቅ ስጋት ያለባቸው ቦታዎችን እየለየ መሆኑን አስታወቀ

የድርቅ አደጋ ሥጋት ያለባቸውን አካባቢዎች የመለየት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን  የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ከሕዳር 7/2009 ዓመተ ምህረት. ጀምሮ 23 ቡድኖችን በ246 ወረዳዎች በማሰማራት የዳሰሳ ጥናት እያከናወነ ነው፡፡

ጥናቱ ሕዳር 30/2009 ዓመተ ምህረት እንደሚጠናቀቅና በተመረጡ ሁሉም ወረዳዎች ከተረጋገጠ በኋላ የበልግ ድርቅ ሁኔታዎችን የሚያሳይ የሰብዓዊ እርዳታ ሰነድ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል ፡፡

በዚህም የሀገሪቱ የሰዎችና የከብቶች ጤንነት፣ የእርሻ ፣ የትምህርት ፣ የሰዎችና የእንስሳት የመጠጥ ውሃ ሁኔታ እንደሚታወቅ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም ምን ዓይነት ድጋፍ ለምን ያህል ሰዎችና እንስሳት ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ማወቅ ይቻላል ነው ያሉት ፡፡

በተጨማሪም የኤልኒኖ ድርቅ ስጋት የሚከሰት ከሆነም በጥናቱ ማረጋገጥ እንደሚቻል አመልክተዋል ፡፡

ኢትዮጵያ የኢልኒኖ ድርቅ ስጋት ግን እነደሌለባትና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥርም እደሚቀንስ መረጃዎች ይጠቁማሉ ነው ያሉት ፡፡

ቀደም ሲል በተደረገው የመኸር ጥናት ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑት ዜጎች ብዛት 10ነጥብ2 ሚሊየን ሕዝብ እንደነበረና አሁን ላይ ወደ 9ነጥብ7 ሚሊየን መቀነሱን ጠቅሰዋል ፡፡

መንግስት እስካሁን ድረስ 16 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በመመደብ ለኤልንኖ ድርቅ የተጋለጡ ዜጎችን የምግብና ምግብ ነክ፣ ጤና፣ ትምህርትና ውሃ ድጋፎችን በማቅረብ በሰዎችና በእንስሳት ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር እያቃለለ መሆኑ ታውቋል፡፡