የማታለልና የውንብድና ወንጀል የፈፀሙ በእስራት ተቀጡ

በአማራ ክልል የማታለልና የውንብድና ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች በእስራት መቀጣታቸውን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ የቀበሌ 02 ነዋሪ የሆነው ሞላ ፍላቴ ቦጋለ ወደ ውጭ አገር እልካችኋለው በማለት ከሰዎች ላይ ገንዘብና ቁሳቁስ መቀበሉ በማስረጃ ተረጋግጦ ጥፋተኛ ተብሏል፡፡

ተከሳሽ የሰዎችን የተሳሳተ እምነት ምክንያት በማድረግ ‹‹አውቅላችኋለሁ፣ እጠነቁልላችኋለሁ፣ እድላችሁን እገልፅላችኋለሁ፣ ከበሽታችሁ እፈውሳችኋለሁ›› በማለት ገንዝበ ተቀብሏል፡፡

ገንዘብ እንደሚያባዛ በማሳመንም 52 ግለሰቦች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፍኖተ ሰላም ቅርንጫፍ የባንክ ሂሳብ እንዲከፍቱ ማድረጉ በክሱ ተመልክቷል፡፡

ተከሳሽ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 598/1 በመተላለፍ በፈፀመው በህገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን ወደ ውጭ ሀገር የመላክና አንቀፅ 700/1ን በመተላለፍ የህዝብን እምነት ተጠቅሞ የማታለል ወንጀል መፈፀሙ በማስረጃ በመረጋገጡ ክስ ተመስርቶበት ጥፋተኛ ተብሏል፡፡

ተከሳሽ ፍርድ ቤት ቀርቦ ወንጀሉን አለመፈፀሙን ክዶ በመከራከር የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም በማስረጃነት የቀረቡትን የሰው ምስክሮች፣ የጥንቆላ ተግባሩን የሚያሳይ ሁለት ፎቶ ግራፍ፣ በእጁ የተገኙ 52 የቁጠባ ደብተሮች፣ ሁለት ፓስ ፖርት፣ በጥንቆላ ተግባሩ በስጦታ መልክ የተሰጠው የወርቅ፣ የብር እና አርቴፊሻል ጌጣ ጌጦች ተገኝተዋል፡፡

ከዚህ በፊት በሌላ የወንጀል ድርጊት አለመከሰሱና የበርካታ ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑ በቅጣት ማቅለያነት ተይዞለት ጥቅምት 15 ቀን 2009 ዓ.ም የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍኖተ ሰላም ከተማ በዋለው ተዘዋዋሪ ችሎት በ5 አመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራትና በ7,000.00(በሰባት ሺ) ብር እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡

በተያያዘ ዜናም በደንቢያ ወረዳ ፈንታይና ሪቻቻ ቀበሌ ምንችራ በሚባል አካባቢ ተከሳሽ ካልታወቀውና ለጊዜው ካልተያዘው ግብረ አበሩ ጋር በመሆን የግል ተበዳይ አግማስ አዲስ ለበሬ መግዥያ የያዘውን አምስት ሺ ብር አፉን በፎጣ አፍኖ ተቀብሎ ሊሰወር ሲል እጅ ከፍንጅ ተይዟል፡፡

ተከሣሽ ፍርድ ቤት ቀርቦ የወንጀል ድርጊቱን እንዳልፈፀመ በመናገር የእምነት ክህደት ቃሉን ቢሰጥም  ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ባቀረባቸው የሰው ማስረጃዎች አረጋግጦ ጥፋተኛ ብሎታል፡፡

ድርጊቱን በግብረ አበርነት መፈፀሙ በቅጣት ማክበጃነት፤ የቤተሰብ አስተዳዳሪና ከዚህ በፊት ሪከርድ የሌለበት መሆኑ ደግሞ በማቅለያነት ተይዞለት የሰሜን ጎንደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥቅምት 15 ቀን 2ዐዐ9 ዓ.ም በዋለው ችሎት በ2 ዓመት ፅኑ አሥራት እንዲቀጣ ወስኗል፡