tህገ መንግስቱ ብዝሃነትን በአግባቡ በማስተናገድ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላምን ከማስፈን ባለፈ ለሀገራችን ህዳሴ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ አስገነዘቡ ።
ፕሬዚዳንቱ የ11ኛውን የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሀገራችን ህዝቦች የቀደመ የተዛባ ግንኙነትን በማረም በመቻቻል ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነትን በማዳበር ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ፕሬዚዳንቱ ህገ መንግስቱ በሀገራችን ያለውን የብዙ ማንነቶች፣ ቋንቋዎች እና ሃይማኖቶች በአግባቡ ማስተናገዱ የስጋት እና የጦርነት ስጋትነታቸውን አስወግዶ የጠንካራ አቅም እና ሰፊ የገበያ እድል መፍጠሩንም ነው የገለጹት።
ፕሬዚዳንት ሙላቱ ህገ መንግስቱ የጸደቀበት ህዳር 29 ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለቀጣይ የህዳሴ ጉዞ ቃላቸውን የሚያድሱበት ቀን መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ያለፉት ሁለት አስርት አመታት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ሲናፍቁት የነበረው የማንነት እና የእኩልነት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በእነዚህ አመታት ዜጎች ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብሮላቸዋል፤ የግል እና የቡድን መብቶቸውም ቦታ ማግኘታቸውንም እንዲሁ።
ዜጎች ህገ መንግስቱ የፈጠረላቸውን መልካም እድል በመጠቀም በመካከላቸው የነበረውን የተዛባ ግንኙነት በማረም
በመከባበር፣ በመቻቻልና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ አንድነት እያጎለበቱ መምጣታቸውንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ህገ መንግስታዊ የጋራ እሴቶችን በመጠበቅ እጅግ በርካታ ስኬታማ ውጤቶችን በማስመዝገብ የቱሩፋቶቹ ተቋዳሽ መሆን መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
ህገ መንግስቱ ከፀደቀ በኋላ ኢትዮጵያ በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ስኬቶችን ማስመዝገብ ብትችልም የመልካም አስተዳደር፣ ሙስና እንዲሁም የሀይማኖት አክራሪነት የሀገሪቱ የህዳሴ ጉዞ ሳንካዎች መሆናቸውን አስገንዝበዋል ።
ፕሬዚዳንት ሙላቱ የህዝቡ ዲሞክራሲያዊ ጥያቄ በስተጀርባ ህገ መንግስቱን በሃይል ለመናድ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ብዝሃነት የችግር ምንጭ አድርጎ በማቅረብ እና ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እርስ በእርስ እንዲጋጩ ልዩነት በመፍጠር ከውጭ ሃይሎች ጋር ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈም የታላቁ የህዳሴ ግድብን ለማስቆም ሲጥሩ ታይተዋል፤ ይሁንና ይህ ጥረታቸው በሰላም ወዳዱ ኢትዮጵያዊ ሊከሽፍ ችሏል ነው ያሉት ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ህዝቡ በተለይም ወጣቱ የእነዚህ ሃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን አሳስበዋል-(ኤፍ.ቢ.ሲ) ።