የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ዜጎች የማንነት መገለጫ የሆነውን ህገመንግስቱን ከማንኛውም አደጋ ለመጠበቅ ቃላቸውን የሚያድሱበት ዕለት መሆኑ ተመለከተ፡፡
ዛሬ በሀረሪ ክልል በተከበረው 11ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ላይ እንደተገለፀው ለዘመናት የህዝቦች ጥያቄ ምላሽ የሰጠውን ህገ መንግስት ከአደጋ መጠበቅ የህዝቦች ኃላፊነት ነው፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ ባደረጉት ንግግር
ህገ መንግስቱንና ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ለመናድ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎችን ዕኩይ ድርጊት ለመከላከል ህዝቦች በተጠንቀቅ መቆም አለባቸው፡፡
በቅርቡ በአገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች ጥቂት የጥፋት ኃይሎች ድብቅ አጀንዳቸውን ለማስፈፀም ያደረጉት ሙከራ በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ መክሸፉን አፈ ጉባዔው አስታውሰዋል፡፡ ህዝቡም ፀረ ሠላም ኃይሎችን በመቃወም ለሠላምና ለልማት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አረጋግጧል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞው ገናናዋ እንድትመለስ የተጀመረው የህዳሴ ጉዞ ዕውን እንዲሆን ህዝቦች በመቻቻልና ዲሞክራሲያዊ አንድነትን በማጠናከር ለልማት እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
‹‹በዓሉ መንግስት ለህዝቡ ጥያቄዎች ተጨባጭ መልስ ለመስጠት ከምንግዜውም በላይ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት መከበሩ የተለየ ያደርገዋል›› ያሉት ደግሞ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙራድ አብዱልሀዲ ናቸው፡፡
የክልሉ መንግስት ለበዓሉ ዝግጅት በርካታ ልማቶችን ማከናወኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ እነዚህም የክልሉን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገትን ለማፋጠን ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል፡፡
የፍቅር፣የሠላምና የመቻቻል ተምሳሌት የሆነችው ሐረርን የቱሪስት መዳረሻና የንግድ ማዕከል ለማድረግ በዓሉ መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላቸውም አቶ ሙራድ አስገንዝበዋል፡፡ በለውጥ ጎዳና ላይ የምትገኘውን ታሪካዊ ከተማ ዕድገት ለማፋጠን የክልሉ መንግስትና ህዝብ እጅ ለእጅ ተያይዘው እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የተፈጠረውን ከፍተኛ ንቅናቄ በመጠቀም ለዘመናት የቆየውን የሠላምና የመቻቻል አኩሪ ዕሴትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣የሱዳንና የጅቡቲ ፕሬዚዳንቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡
የዘንድሮ በዓል ‹‹ህገ መንግስታችን ለዲሞክራሲያችንና ለአንድነታችን›› በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡