የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ከገቢ ባሻገር ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ከፍተኛ ገቢ ከማስገኘት በተጨማሪ ትልቅ ልማታዊ መነቃቃትን መፍጠሩ ተገለፀ፡፡

በየዓመቱ በተለያዩ ክልሎች የሚዞረው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ገቢ ከማሰባሰብ በተጓዳኝ መነቃቃትን በመፍጠር የህዝቡን ልማታዊ ተሳትፎ እያሳደገ መሆኑ ነው የተመለከተው፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖችና ከተሞች በመዘዋወር ገቢ ሲያስገኝ የነበረውን ዋንጫ ዛሬ በሀረሪ ክልል በተከበረው 11ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የደቡብ ብሄሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ተረክቧል፡፡

ዋንጫው በኦሮሚያ ክልል በነበረው የአንድ ዓመት ቆይታ የክልሉ ህዝብና መንግስት የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ እንደ ትልቅ መሳሪያ በመጠቀም ገቢ ማሰባሰቡን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ገልጸዋል፡፡

ዋንጫውን በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ከተማዎች በማዘዋወር ለግንባታው ድጋፍ ለማሰባሰብ በተደረገው ጥረት 607 ሚሊዮን 347 ሺ 813 ብር መገኘቱን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ለግድቡ ግንባታ ዕውን መሆን ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት ፡፡

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ የክልሉ ህዝብ በቦንድ ግዥና በስጦታ በአጠቃላይ 1 ቢሊዮን 671 ሚሊዮን 188ሺ 241 ብር ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስም የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ዋንጫውን የተረከበው የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የክልሉን ህዝብ በማስተባበር የተሻለ ገቢ ለማሰባሰብ እንደሚንቀሳቀስ አመልክቷል፡፡

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ደሴ ዳልኬ ዋንጫው ወደ ክልሉ መምጣቱ ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ ህዝብም የአገሪቱን ህዳሴ ለማረጋገጥ የተጀመረው ጉዞ ከዳር እንዲደርስ የበኩሉን ድጋፍ በማድረግ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡