የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት የተለያዩ ሹመቶችን አፀደቀ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የተለያዩ ሹመቶችን በማፅደቅ ስብሰባውን አጠናቀቀ።

ምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ የነበሩትን አቶ ወልደ ገብርኤል አብርሃን በአቶ ተስፋዬ ተርፋሳ ተክቷቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በከንቲባ ድሪባ ኩማ የቀረቡለትን ስምንት የስራ አስፈጻሚ አመራሮችን ሹመት ተቀብሎ አፅድቋል።

ዶክተር ጀማል አደም ዑመር የጤና ቢሮ ሃላፊ፣

አቶ ማቲዎስ አስፋው የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር፣

ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ የመንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ፣

አቶ መሃመድ አህመዲን የትምህርት ቢሮ ሃላፊ፣

አቶ ዘርዑ ሱሙር የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ሃላፊ፣

አቶ ልዑልሰገድ ይፍሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሃላፊ፣

አቶ ለዓለም ተሰራ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሃላፊ፣

አቶ ዲላሞ ኦቶሬ የንግድ ቢሮ ሃላፊ በማድረግ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ የ14 ዳኞችና የሶስት ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሰብሳቢ ሹመትንም ተቀብሎ አጽድቋል።

በተጨማሪም አዲስ አበባን በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር እና ለመምራት ያስችላል ተብሎ የሚጠበቀውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፕላን ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ እና የማሰልጠኛ ተቋማትን በስሩ ለማቋቋም በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

ለምክር ቤቱ አዲስ ስምንት ስራ አስፈጻሚዎችን በማቅረብ ያፀደቁት የከተማዋ ከንቲባ ድሪባ ኩማ በ2008 ዓ.ም ከተቋቋሙት ዘጠኝ የስራ አስፈጻሚ አመራሮች ውስጥ ሰባቱ የቢሮ ሃላፊዎች እንዲቀጥሉ መወሰኑን ተናግረዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ፣ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ነባር ሃላፊዎች ባሉበት እንዲቀጥሉ መወሰኑንም ነው የተናገሩት።

ከንቲባው አዲስ የከተማ ማስተር ፕላን ተጠንቶ በመጠናቀቁ ምክንያት አራት የማስተር ፕላን ማስፈፀሚያ ተቋሞች ይቋቋማሉም ብለዋል።

በቅርቡም የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አደረጃጀትና አሰራር ላይ እየተደረገ ያለው ጥናት ሲጠናቀቅም የማዘጋጃ ቤታዊ አደረጃጀቱ በአዲስ መልክ ይደራጃል ነው ያሉት።(ኤፍቢሲ)