ምክር ቤቱ የተለያዩ የብድር ስምምነቶችን ለቋሚ ኮሚቴ መራ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ የብድር ስምምነቶችን ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጆችን ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ከአበዳሪ ተቋማት የተገኙ ስድስት የብድር ስምምነቶችን ለበጀትና ፋይናስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

የብድር ስምምነቱ ለመንገድ ልማት፣ለኤሌክትክ ኃይል ማስፋፊያ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን ባቡር መስመር ዝርጋታ፣ ለብሔራዊ የኃይል አቅርቦት መቆጣጠሪያ ማዕከል ፕሮጀክት ማስፋፊያ የሚውሉ ናቸው፡፡

ከፑሽኪን አደባባይ እስከ ጎተራ ማሳለጫ ያለውን መንገድ ለመገንባት ከቻይና መንግስት ከወለድ ነፃ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብድር ተገኝቷል፡፡ የአዲስ አበባን የጥራፊክ መጨናቀቅ ያቃልላል፡፡

ከቃሊቲ የቀለበት መንገድ አደባባይ እስከ ቱሉ ዲምቱ አደባባይ፤ እንዲሁም ከቃሊቲ የቀለበት መንገድ በቡልቡላ እስከ ቂሊንጦ አደባባይ ለሚገነቡ መንገዶች ከቻይና ኤግዚም ባንክ 102 ሚሊዮን 736 ሺ 147 ብር ተገኝቷል፡፡ ለፕሮጀክቱ በአጠቃላይ ከሚያስፈልገው ከአራት ሚሊዮን ብር ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይሸፈናል፡፡

ለሀሙሲት-እስቴ መንገድ ፕሮጀክት ከአረብ ባንክ አንድ በመቶ ወለድ የሚታሰብበት የ15 ሚሊዮን ዶላር ብድር መገኘቱ ለምክር ቤቱ ተገልጿል፡፡ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው ተጨማሪ 29 ሚሊዮን ዶላር በኦፔክ ፈንድና በኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሸፈን ነው የተመለከተው፡፡

ሌላው የብድር ስምምነት ለአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን አውቶቡስ መስመር ዝርጋታ የሚውል ነው፡፡ ለዚህም ከፈረንሳይ የልማት ኤጄንሲ 35 ሚሊዮን ዩሮ የተገኘ ሲሆን ይህም ቀደም ሲል ኤጄንሲው ከሰጠው 50 ሚሊዮን ዩሮ በተጨማሪነት የተገኘ ነው፡፡

ለዚህ ፕሮጀክት ከሚያስፈልገው 101 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዩሮ ከፈረንሳይ የልማት ድርጅት የተገኘው 85 በመቶውን ይሸፍናል፡፡ ብድሩ ለመሰረተ ልማት ግንባታና ለመሳሪያዎች አቅርቦት ይውላል፡፡

ኤጄንሲው ለብሔራዊ የኃይል አቅርቦት መቆጣጠሪያ ማዕከል ፕሮጀክትም 40 ሚሊዮን ዩር በብድር ሰጥቷል፡፡ በዚህም የኃይል መቆጣጠሪያና የመጠባበቂያ መቆጣጠሪያ ማዕከላትና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ይከናወናሉ፡፡

ለአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መረብ ማሻሻያና ደረጃ ማሳደጊያ ፕሮጀክት በአጠቃላይ ከሚያስፈልገው ከ274 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው ከቻይና ኤግዚም ባንክ በብድር መገኘቱ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም በዓመት ሁለት በመቶ ወለድ የሚታሰብበት 230 ሚሊዮን ዶላር በብድር ተገኝቷል፡፡

ብድሮቹ ከአምስት እስከ 10 ዓመት የእፎይታ ጊዜ የተቀመጠላቸው ሲሆን ከ20 እስከ 30 ዓመት ተከፍለው የሚጠናቀቁ ናቸው፡፡ ከወለድ ነፃን ጨምሮ የወለድ መጠናቸውም በጣም አነስተኛ መሆኑ ተመልክቷል፡፡