በስዊዘርላንድ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ለ11ኛ ጊዜ በድምቀት መከበሩን በስዊዘርላንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡
በዓሉን በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን “ህገ-መንግስታችን ለዲሞክራሲ አንድነታችንና ለህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል ማክበራቸው ተገልጿል፡፡
በዓሉ የህዝቦች እኩልነት፣ አብሮ የመኖርና የመቻቻል ዕሴቶችን ለማጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው በስዊዘርላንድ የኢፌዲሪ ቋሚ መልዕክተኛ ተወካይ አቶ ዮሴፍ ካሳ ገልፀዋል፡፡
የዘንድሮ በዓል ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር የተሀድሶ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ባለበት ወቅት መከበሩ የተለየ እንደሚደርገው ተወካዩ ተናግረዋል፡፡
‹‹ልዩነታችን ጌጥና ውበት ከመሆኑም በላይ የጥንካሬያችን ምንጭ እና የአንድነታችን ምሰሶ መሆኑን በተግባር ማየት ተችሏል›› ያሉት ተወካዩ ተከታታይና ፈጣን ዕድገትን ማስመዝገብ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባትና ቀድሞ ወደ የነበረችበት የስልጣኔ ማማ ለማውጣት የህዳሴ ጉዞው ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ ዮሴፍ አስረድተዋል፡፡
መንግስት የጀመረው የህዳሴ ጉዞና የልማት ስራዎች ዕውን እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
መንግስት ለህዝቡ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ቀልጣፋና ፍትሃዊ አስተዳደር በተሻለ ደረጃ ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት የኢትዮጵያ ዳያፖራዎች በእውቀትና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አዳዲስ አሰራሮችና የሙያ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትጵያዊያን የጠባብነትና የትምክህት አስተሳሰቦች ሰለባና መሳሪያ ከመሆን ተቆጥበው በጥፋት ሀይሎች የሚከናወኑ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን በማጋለጥ የሰላም አምባሳደርነት ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል፡፡
የበዓሉ ተሳታፈዎች በበኩላቸው በዓሉ የኢትዮጵያዊነት መንፈስን ለማጠናከር፣ እኩል ተሳትፎና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ፣ የተገኙ ድሎችን አጠናክሮ ለመቀጠልና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ቃላቸውን የሚያድሱበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና ሕብረብሔራዊነት በኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት›› በሚል ርዕስ ገለፃና ውይይት ተደርጓል፡፡ በሐረሪና በኢትዮጵያ ሶማሌ ኮሚኒቲ የተዘጋጀ ባህላዊ ምግብ የቀረበ ሲሆን በኮሚኒቲው የሴቶች ሊቀ መንበር ወይዘሮ ሰዓዳ ፈሲህ ዝርዝር ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ የሻማ ማብራትና የዳቦ ቆረሳ ሥነ-ስርዓት ተካሄዷል፡፡