ሚኒስትሩ የዕድገት ስራዎችን መረጃ በተደራጀ መልኩ ማቅረብ እንደሚገባ አስገነዘቡ

የዕድገትና የልማት ስራዎች በተደራጀ መልኩ ለህብረተሰቡ ማቅረብ እንደሚገባ የፌዴራል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈትቤት ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አስገነዘቡ፡፡

ሚ ኒስትሩ ይህንን ያስገነዘቡት ትናንት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያዘጋጀውን የ2008 በጀት ዓመት ዓመታዊ መጽሐፍ ባስመረቀበት ወቅት ነው ፡፡

ሚኒስትሩ በመንግስትና ሕዝብ የተከናወኑ የዕድገትና ልማት ሥራዎችን ለሕብረተሰቡ በመረጃ አስደግፎ ማቅረብ  ስኬታማ ሥራዎችን ለማከናወን  ይበልጥ የሚያሳሳ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

ስለሆነም  መረጃን በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ ለሕብረተሰቡ ማድረስ ይገባል ብለዋል ፡፡

ዜጎችን የሚጠቅሙ መልካም ነገሮችና ችግሮች በሚዛናዊነት ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ በሕብረተሰቡና በመንግስት መካከል ያለውን የመረጃ ክፍተት ከመሙላቱ በሻገር የህብረተሰቡን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ እንደሚያስችልም ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው አስተዳደሩ በተለያዩ ዘርፎች ያከናወናቸውን ተግባራትን በመመርኮዝ መረጃዎች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ዓመታዊ መጽሐፉ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የመረጃ ተደራሽነት ከሚከወንባቸው የኮሙኒኬሽን አግባቦች አንዱ በሆነው ዓመታዊ መጽሐፍ የአስተዳደሩን ሥራዎች ለህብረተሰቡ በግልጽ መረጃ የማቅረቡ ተግባርም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ዓመታዊ መጽሐፉ በከተማዋ ሁሉም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በማህበራዊ፣ መሰረተ ልማት፣ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ በ2008 በጀት ዓመት የተከናወኑ አብይ ተግባራትን ማካተቱን  ነው የተመለከተው ፡፡

መጽሐፉ ለነዋሪዎች፣ ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለተመራማሪዎች ለኤምባሲዎች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ለሲቪክ ማሕበራት፣ ለጋዜጠኞችና መረጃ ለሚሹ ሁሉ  እንደተጨማሪ የመረጃ ምንጭነት እንደሚያገለግል ጠቁመዋል ።

ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የታተመው ዓመታዊ መጽሐፉ በመዲናዋ የሚገኙ 10 ክፍለ ከተሞችንና 117 ወረዳዎችን የሥራ አፈፃጸም በ454 ገጾችና በ3ሺህ 500 ቅጂዎች አካቶ የታተመ መሆኑን ነው የተመለከተው   ፡፡

አዲስ አበባ ከተማ የተቆረቆረችው በአጼ ሚኒሊክ የንግስና ዘመን በ1879 ዓመተ ምህረት ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ 7ሚሊየን የሚጠጋ ሕዝብ እንደሚኖርባት መታወቁን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡