አገሪቱን 1ነጥብ5 ቢሊዮን ብር አሳጥተዋል በሚል የተጠረጠሩ 28ግለሰቦች ማሰሩን ፖሊስ አስታወቀ

በሀሰተኛ የቡና ንግድ ፈቃድ አገሪቱን ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ አሳጥተዋል በሚል የተጠረጠሩ 28 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ።

በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግለሰቦች አራቱ ነባር የቡና ላኪነት ፍቃድ ያላቸው ባለሀብቶች እና
አምስቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ግብይት ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች መሆናቸውን ነው ያመለከተው ።

ከ2000 እስከ 2007 ዓም ተፈፀመ በተባለው በዚህ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ግብይት ባለስልጣን የቡና ጥራትና ቁጥጥር ዳይሬክተርና የቡና ቁጥጥር ቡድን መሪው እንዲሁም የባለ ስልጣኑ ሶስት ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ተጠቃሾች መሆናቸውን ገልጿል ።

በተለይም ጌታሁን ቢኮራ እና ታጠቅ ግርማ የተባሉ ግለሰቦች በንግድ ሚኒስቴር የቡና እና ሻይ ገበያ ከ2000 እስከ 2007 ዓ.ም በስራ ሃላፊነት ተመድበው ሲሰሩም መንግስት የሰጣቸውን ስልጣንና ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከነጋዴዎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ከ56 በላይ ቡና ነጋዴ ባለሃብቶች ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቡና ገዝተው በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ በኩል ወደ ውጭ ሃገር እንዲላክ ቁጥጥር ማድረግ ሲገባቸው አለማድረጋቸውን ነው ፖሊስ የገለፀው።

በዚህም ሃገሪቱ ከ56 ነጋዴዎች በላይ ለሰባት ዓመታት ቡናውን ወደ ውጭ ቢልኩ ኖሮ ይገኝ የነበረውን ከ75 ሚሊየን 686 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አሳጥተዋል በሚል ተጠርጥረው የፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ሰር አውሏቸዋል።

ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ የወንጀል ችሎት በማቅረብም ምርምራውን በሰውና በሰነድ ማስረጃ በስፋት ለማጣራት ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በፖሊስ የተጠረጠርንበት ጉዳይ ቀድሞ ክፍተቱ እንዳለ በማጥናት 56 ነጋዴዎች በትክክል የተቀበሉት ቡና ወደ ውጭ እንደማይልኩ ለይተን ያዘጋጀነውና ማስተካከያ እንዲወሰድ የጠየቅነው እኛ ነን፤ ክፍተቱን አጥንተን መፍትሄውን ማዘጋጀታችን አያስጠረጥረንም ብለዋል ለፍርድ ቤቱ።

ፖሊስ የስራ ሃላፊዎቹ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸውና ከነጋዴዎች ጋር በነበራቸው መመሳጠር የተፈጠረ በመሆኑ የኦዲት ሪፖርትን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን እየለየ እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ሲጠይቁ ፖሊስ የጀመርኩትን ምርመራ መረጃ በመደበቅ ያደናቅፉበኛል፤ ሌሎች ተጠርጣሪዎች መረጃ እንዲያሸሹ ያደርጋል በማለት የዋስትና መብት እንዳይፈቀድ ጠይቋል።

የግራና ቀኙ ክርክር ያደመጠው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ ተጨማሪ የ8 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።