ምክርቤቱ ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ጭማሪና ለሌሎች ተግባራት የሚውል ተጨማሪ በጀት አጸደቀ

ምክር ቤቱ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ጭማሪና ለሌሎች ተግባራት የሚውል  18ነጥብ26 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ

ለመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ የሚውል ተጨማሪ በጀት አጸደቀ ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ በአገር ዓቀፍ ደረጃ የመንግስት ሠራተኞችን  ከጥር 01 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት  ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ የሚውል 9 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አፅድቋል፡፡

የደመወዝ ጭማሪው በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ላይ ለመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደረግ መንግስት በወሰነው መሰረት የተከናወነ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ለፌዴራል መንግስት ለ2009 ዓ.ም 18 ነጥብ 26 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀትን ነው መርምሮ ያጸደቀው ፡፡

ተጨማሪ በጀቱ ለመደበኛና ለካፒታል ወጭዎች የሚውል መሆኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

የፀደቀው በጀት ከጥር ወር ጀምሮ ተግባራዊ ለሚሆነው የመንግስት ሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪ፣ ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ፣ ለገጠር ልማታዊ የሴፍትኔት ፕሮግራም፣ ለከተማ የምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት፣ለጥቁር አንበሳ የልብ ህክምና ማዕከል ግንባታና በጉሙሩክና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት የሚውል መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በዚህም መሰረት ለደመወዝ ጭማሪ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር፣ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማሳደግ ለታቀደው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ  ከተወሰነው 10 ቢሊዮን ብር ውስጥ ለግማሽ ዓመት አምስት ቢሊዮን ብር፣ በገጠር ለሚካሄደው ልማታዊ የሴፍትኔት ፕሮግራም፣ ለድርቅ መከላከያና የመንግስት ግዴታዎችን ለመወጣት 3ነጥብ 91 ቢሊዮን ብር ወጭ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከኔዘርላንድስ መንግስት በሚገኝ እርዳታ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለሚገነባው የልብ ህክምና ማዕከል የመንግስት ድርሻ 90 ሚሊዮን ብር፣ ለከተማ ምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍትኔት 236 ነጥብ 25 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የጉሙሩክና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን ለማሳለጥ የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመስጠት የሚያችል ሥርዓት ለመዘርጋት 20 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ለምር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ተጨማሪ በጀቱን ለመሸፈን የሚያስፈልገው ተጨማሪ ገቢ ታክስ ካልሆኑና ከካፒታል ገቢዎች እንደሚሸፈን  ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በተለይም ታክስ ካልሆኑ ከዘቀጠ ትርፍ አንድ ነጥብ 33 ቢሊዮን ብር(ከብሔራዊ ባንክ አንድ ቢሊዮን ብር፣ ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅት 200 ሚሊዮን ብር፣ ከልማት ባንክ 130 ሚሊዮን ብር)፣ ከነዳጅ ማራገፊያ ፈንድ 10 ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገቢ ይሰበሰባል፡፡

ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ሽያጭ 6 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር እና ከሌሎች ልዩ ልዩ ገቢዎች 188 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ገቢ እንደሚኖር በተደረገው ማጣራት መረጋገጡን ሚኒስትር ዴአታው ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘም ዜናም ከኃላፊነት ለሚነሱ የሀገርና የመንግስት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች የሚያገኙዋቸውን መብቶችና ጥቅሞች ለመወሰን የተዘጋጀውን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ የፓሪስ ስምምነትን ለማፅደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አፅድቋል፡፡

ምክር ቤቱ በስድስት ወራት ያከናወናቸውን ዋና ዋና የፓርላማ ዲፕሎማሲ ሪፖርት አድምጧል፡፡