ምክርቤቱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ 6ኛ ዓመትን ለማክበር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገለጸ

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 6ኛ ዓመት ለማክበርም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት አስታወቀ ፡፡

የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አብርሃም ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት ፤በታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ መሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበት ዕለት ብልዩ ልዩ ዝግጅቶች ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት ተጀምሯል ፡፡

የቁንጅና ውድድር፣ አውደ ርዕይ፣ ቶክ ሾው፣ የሕፃናት የሥዕል ውድድር፣ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችና ፓናል ውይይቶች ብሔራዊ መግባባትንና ገቢ ማሰባሰብን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በበዓሉ ላይ ትኩረት የተሰጣቸው ፕሮግራሞች  መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያዎች የሚካሄዱ ሲሆን፤“ለእናቴ፣ ለእህቴና ባለቤቴ እሮጣለሁ” በሚል መርህ የሚካሄደው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሩጫም እንደሚካሄድ ነው ያስታወቁት ፡፡

ቀደም ሲል ከሕዳሴው ግድብ ሎተሪ 64 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ገቢ መደረጉን አንስተው፤ በቀጣይም የቶምቦላና የዳያስፖራ ሎተሪ ለማዘጋጀት መታቀዱን አመልክተዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በሚገኙባቸው አገራት ቆንስላዎች በዓሉን በውይይቶችና የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶችን በማካሄድ ለማክበር እየተዘጋጁ እንደሆነ ታውቋል፡፡

አርሶአደሩንና አርብቶ አደሩን በበዓሉ ላይ ተሳታፊ በማድረግ ለግድቡ በሚደረገው ተሳትፎ ይበልጥ ማነቃቃትና ማጠናከር የሚቻልበትን ሁኔታ ትኩረት እንደተሰጠው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል እየተደረገ ያለው የፐብሊክ ግንኙነትም ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ኃላፊው ፤የሱዳንና ኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ማህበርም የዚህ ማሳያ መሆኑ አስረድተዋል፡፡  

በተለይም ከሁሉም የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር የሚኖረውን ግንኙነቱን አጠናክሮ ለመቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ፡፡