ጠ/ሚ ኃይለማርያም ከስዊዘርላንድ ፕሬዚዳንት ጋር መከሩ

ኢትዮጵያ ታዳሽ ሃይልን በመጠቀምና አረንጓዴ ልማትን ማዕከል ያደረገ የዘላቂ ልማት ስራዎችን በማከናወን ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዳቮስ ከስዊዘርላንድ ፕሬዚዳንት ዶሪስ ሊውተርድ ጋር በዳቮስ ባደረጉት ውይይት፤ የስዊዘርላንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ ኢንቨስትመንት እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የስዊዘርላንድ ፕሬዝዳንት ዶሪስ ሊውተርድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ስደተኞችን በመቀበልና በዘላቂነት የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል።

መሪዎቹ በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት በተለይም ከስዊዘርላንድ ጋር ባለው የንግድ እና ኢንቨስተመንት ግንኙነት እንዲሁም አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ረዳት አቶ እውነቱ ብላታ ለኢቢሲ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ስደተኞችን በመቀበልና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማድረግ የምታከናውናቸውን ሰራዎች ስዊዘርላንድ እንደምትደግፍ ፕሬዚዳንት ዶሪስ ሊውተርድ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገልጸውላቸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ጸጥታን ለማስጠበቅ ረገድ ባላት ሚና ላይም ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን አቶ እውነቱ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የስዊዘርላንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በሚያፈሱበት ሁኔታ ላይ ለፕሬዚዳንቷ ገለፃ አድርገውላቸዋል።

ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን የሚጠቀምና አረንጓዴ ልማትን መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎችን በማካሄድ ግንባር ቀደም ተግባር እያከናወነች ትገኛለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ የካርበን ልቀትን የቀነሰ ኢኮኖሚን እየገነባች መሆኑን ገልጸዋል።

ስዊዘርላድም ይህን የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም እንደምትደግፍ ፕሬዚዳንት ዶሪስ ሊውተርድ ማረጋገጣቸውን አቶ እውነቱ ጠቁመዋል።

ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ ከ60 አመት በላይ ያስቆጠሩት ኢትዮጵያ እና ስዊዘርላንድ ዘርፈ ብዙ የሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ታሪክ እንዳላቸው ይታወቃል ፡፡