ኮማንድ ፖስቱ በሁከቱ የተሳተፉ አካላት አድኖ መያዝን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ  

ኮማንድ ፖስቱ በሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈው ያልተያዙ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያደርገው ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ ፡፡

 

ኮማንድ ፖስቱ በሀገሪቱ ተከስቶ በነበረው ነውጥ ተሳታፊ የነበሩ እስካሁንም ያልተያዙ አካላትን አድኖ መያዝን አጠናክሮ መቀጠልን ጨምሮ ሌሎች አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የሶስት ወር አፈጸጸም ግምገማውን ትናንት አጠናቋል ።

የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት እና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ከአስቸኳይ አዋጁ በኋላ በመላ ሃገሪቱ አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን አረጋግጠው ፤ አሁንም አልፎ አልፎ የጸጥታ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል ።

ስለሆነም ኮማንድ ፖስቱ በሁከት እና ነውጥ ተሳትፈው ያልተያዙትን በቁጥጥር ስር ለማዋል አሁንም ተጨማሪ ስራ ያስፈልጋል የሚል ግምገማም ማስቀመጡን ነው ያስገነዘቡት ።

ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋርም ከአፈጻጸም መመሪያው ባፈነገጠ መልኩ በፍተሻ እና ብርበራ ኬላዎች ከሚሰሩ ስራዎች ጋር ተያይዞ አቤቱታዎች እንደሚቀርቡ ነው የጠቆሙት ።

በመሆኑም በየአካባቢው ያለውን አሰራር የመፈተሽ ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ በህግ የሚጠየቁትን በህግ በስነ-ምግባር የሚጠየቁትን ደግሞ በስነ-ምግባር ተጠያቂ ከማድረግ አንጻር የተሰሩ ስራዎች ቀርበው ተገምግመዋልም ነው ያሉት ።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ኮማንድ ፖስቱ በሀገሪቱ ተከስቶ በነበረው ሁከት እና ነውጥ ተሳታፊ የነበሩ እና እስካሁን በቁጥጥር ስር ያልዋሉ አካላትን አድኖ መያዝን የመጀመሪያው የትኩረት አቅጣጫው አድርጎም ነው ያስቀመጠው።

የክልል ጸጥታ ሃይሎችን ይበልጥ ለማጠናከርም ከክልል መንግስታት ጋር በትብብር የተጀመረውን የማጽዳት፣ መልሶ የማደራጀት እና የማሰልጠን ተግባርን በመፈጸም ጠንካራ አቋም ያለው የጸጥታ ሃይል መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል ።

ኮማንድ ፖስቱ በቀጣይ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ቁጥጥር እና የክልል ጸጥታ ሃይልን ይበልጥ የማጠናከር ስራ ላይ እንዲያተኩርም አመልክተዋል ፡፡

ለመሰረተ ልማቶችና ፕሮጀክቶች የሚደረገውን ጥበቃ በማጠናከር ጥቃት እንዳይሰነዘርባቸው ማድረግ እና የሀገሪቱን ሰላም ዘላቂ ማድረግም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አረጋግጠዋል ።

የህዝቡን ተሳትፎ ይበልጥ በማሳደግ ህዝቡ ራሱ የዘላቂ ሰላሙ መድህን እንዲሆን ማስቻልም ቀጣይ ተግባር ይሆናል ብለዋል ።

ኮማንድ ፖስቱ ሀገሪቱን ወደ ቀደመ ሰላሟ የመመለስ ተግባሩን በአግባቡ መከወኑን ቀዳሚ ስኬት አድርገው አንስተዋል።

በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በተለይም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች፤ ይታይ የነበረው ሁከት እና ግርግር መክሰሙም አንዱ ማሳያ መሆኑን ነው የገለጹት ፡፡

ነውጡን ሲመሩ የነበሩ ቡድኖችን መቆጣጠር መቻሉም ስኬታማ አፈጻጸም የታየበት መሆኑን አረጋግጠዋል ።

በነውጡ ተሳታፊ የነበሩ ዜጎችን በቁጥጥር ስር በማዋል አስተምሮና አርሞ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ተግባር  ውጤታማ እንደነበር ጠቅሰዋል ።

ሀገሪቱን ወደ ቀደመ ሰላሟ በመመለስ ሂደት ውስጥ ህዝቡ የራሱን ሚና እንዲጫወት የማድረጉ ወሳኝ እንደነበር  አቶ ሲራጅ  አስታውቀዋል  ።

ኮማንድ ፖስቱ ግዙፍ የመሰረተ ልማት አውታሮችን፣ፋብሪካዎችንና አገናኝ አውራ ጎዳናዎች ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ያስቻለ ውጤታማ ስራ መስራቱንም አረጋግጠዋል።

በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ሁከት እና ነውጥ በመደበኛ የጸጥታ ማስከበር ሂደት መቆጣጠር ባለመቻሉ ምክንያት የታወጀው አዋጅ አራተኛ ወሩን መያዙ ይታወቃል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።