በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት 4ነጥብ 5 ሚሊዮን  አርብቶ አደሮች  ተጠቃሚ ሆኗል  – አቶ ካሳ ተክለብርሃን

በጅግጅጋ  ከተማ  ዛሬ በተካሄደው 16ኛው  የአርብቶ አደሮች ቀን በዓል ላይ የተገኙት የፌደራልና አርብቶ አደር  ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን ባደረጉት  ንግግር የሰፊ  መሬት ፣ የእንስሳት ሃብት፣የከርሰና  የገጸ ምድር ውሃ  ባለቤት  የሆነው አርብቶ አደሩ  በራሱ መተዳደር  ከጀመረ  በኋላ  የተለያዩ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን መስመዝገቡን ገልጸዋል ።

አርብቶ አደሮች ባለፉት  ሁለት አሥርት ዓመታት በተረጋገጠላቸው  መብቶችን  ማጣጣም በመጀመራቸው   የተለያዩ የፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት  ተጠቃሚ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ፡፡

በአርብቶ አደሩ አካባቢ የአርብቶ አደር  ማህበረሰብ ልማት ፕሮጀክትን ከ1992 ዓም  ጀምሮ   በሦስት  ምዕራፎች  እስካሁን  በ145 ወረዳዎች  ተግባራዊ ተደርጎ 4ነጥብ 5  ሚሊዮን  አርብቶ አደሮችን  የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና አገልግሎቶች ተጠቃሚ ማድረጉን አቶ ካሳ አስታውቀዋል ።

በአርብቶ አደሩ አካባቢ  ድርቅን  በዘላቂነት ለመከላከልና  የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ  ከ 200 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ  የድርቅን ተጋለጭነት ለመቀነስ  የተለያዩ ሥራዎች  በአሁኑ ወቅት በመከናወን ላይ መሆናቸው አቶ ካሳ አመልክተዋል ።

በዚሁም የአርብቶ አደሩ ከሌሎች የአገሪቱ  ህዝቦች  ጋር በመሠረታዊ መለኪያዎች  ተመጣጣኝ ልማት እንዲኖረው   ለማድረግ ዙሪያ  መለስ እንቅስቃሴዎች   ሲደረጉ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይህም የሆነው የፌደራል  መንግሥት  ባቋቋመው  የልዩ ድጋፍ  ቦርድ አርብቶ አደሩ  በመታገዙ መሆኑን አስረድተዋል ።

ይህም ከፌደራል እስከ ክልል አደረጃጃቶችን  በመፍጠር በአርብቶ አደር ክልሎች የሰው ኃይልና አመራሩን  አቅምን  ለማሳደግ  በርካታ ሥራዎች  መከናወናቸውን የጠቀሱት አቶ  ካሳ፤ በተለይ  ሰፊ የማስፈጸም  አቅማቸው  ለማሻሻል ተችሏል ብለዋል ።

አርብቶ አደሩ  በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት  አገልግሎት ተደራሽነት  ረገድ አመርቂ ውጤቶች  ተመዝግበዋል ያሉት አቶ ካሳ፤  አርብቶ አደሩ  ምርቱን ወደ ገበያ  በማውጣት ገቢው  እንዲያድግም አበረታች ውጤቶች  መገኘታቸውን አብራርተዋል  ።

ውሃን  ማዕከል  ያደረገና በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ  የመንደር ማሰባሰብ  ፕሮግራምን ተግባራዊ በማድረግ   ስኬታማ መሆን ተችሏልም ነው ያሉት  ።

እንደ አቶ ካሳ ገለጻ የከርሰ ምድር ውሃ ልማት  ሥራዎች  በተለያዩ  የአርብቶ አደሩ አካባቢዎች ቢጀመሩም  ፈጥነው  አገልግሎት ባለመጀመራቸው በተገቢው መልኩ  ባለመተግበራቸው    የድርቅን  ተጋላጭነት  በሚፈለገው መጠን  መቀነስ እንዳይቻል ማድረጉን ነው ያመለከቱት ።

ስለሆነም በቀጣይ በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃ አቅምን በማሳደግ  የአንስሳት ሃብቱን   በዘመናዊ  መልኩ  ጥቅም ላይ እንዲውል ርብርብ ማድረግ አንደሚያስፈልግ አቶ ካሳ በአጽንኦት አስገንዝበዋል ።

16ኛው  የአርብቶ አደር ቀን በዓል  “ የአርብቶ አደሩ የሰላምና የልማት የላቀ ተጠቃሚነት ለህዳሴያችን  ”  በሚል  መሪቃል  በጅግጅጋ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል ፡