መንግሥት የአርብቶ  አደሮች በዓል በኢጋድ አባል አገራት እንዲከበር   እየሰራ  ይገኛል – ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም

የኢትዮጵያ  አርብቶ አደር ቀን በዓል  በኢጋድ አባላት አገራትም  እንዲከበር ለማድረግ  የኢፌዲሪ መንግሥት  ከሚመለከታቸው አካላት  ጋር በመሆን  የተለያዩ ጥረቶችን  እያደረገ መሆኑን   ጠቅላይ  ሚኒስትር ኃይለማርያም  ደሳለኝ  አስታወቁ  ።

በ16ኛው የአርብቶ አደሮች ቀን በዓል ላይ የተገኙት  ጠቅላይ  ሚኒስትር ኃይለማርያም ባደረጉት  ንግግር በተከታታይ  የአርብቶ አደሮች በዓል ቀን ክፍለ አህጉራዊ ገጽታ እንዲኖረው በኢጋድ አባል አገራት እንዲከበር ለማድረግ መንግሥት  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል ብለዋል ።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገለጻ ፤ ለ16ኛ ጊዜ የተከበረው የአርብቶ አደር ቀን በዓል ድንበር ተሻግሮ በኢጋድ አባል አገራትም እንዲበር ለማድረግ  የሚደረጉት   ጥረቶችን ተጠናክረው ይቀጥላሉ  ።  

የአርብቶ አደር ቀን በዓል የአርብቶ አደሩ የልማት ተጠቃሚነት የሚያጎሉ  ተሞክሮዎችን  የምንለዋወጥበት ነው  ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ በዓሉ  ባለፉት ዓመታት  በአርብቶ አደሩ አካባቢ  ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የተከናወኑ እንቅስቃሴዎችን በመዳሰስ  ለቀጣይ የህዳሴ ጉዞ ልምድ የምናገኝበት ነው ብለዋል ።

የአገሪቱ  የአርብቶ አደር ልማት ፖሊዎችና ስትራቴጂዎች  ዓላማቸው አርብቶ አደሩ በአካባቢው የሚገኙ  ሃብቶች የሆኑትን ፣ ሰፊ የከርሰ ምድር ውሃና የእንስሳት ሃብት  በዘላቂነት  በመጠቀም  የአርብቶ አደር ማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል ።

በተለይ  በፈቃደኝነት ላይ  የተመሠረተው የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም   የአርብቶ አደሩን  በማሳተፍ  ተግባራዊ እየተደረገ  መሆኑንና በአርብቶ አደሩ አካባቢ  ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን ልማትን  በማረጋጋጥ   ረገድ  ስኬታማ  እንደሆነ   ጠቅላይ ሚንስትሩ አመልክተዋል ።

የፌደራልና ክልል መንግሥታት ተቀናጅተው የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን ከመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ጋር በማጣመር የሚያከናውኑት ሥራዎች በአርብቶ አደሩ አካባቢ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ማሳያታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል ።

ፕሮግራሙ የጤና ፣የትምህርት ቤቶች ፣ የመጠጥ ውሃ ተቋማትና በድህነት ቅናሳ  የተቀመጡ ግቦች በማሳካትና የአርብቶ አደሩን  አኗኗር  ሁኔታ ዘመናዊ በማድረግ የኑሮውን ደረጃ ማሻሻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል ።  

አርብቶ አደሩ  ከአንስሳትና ከሰብል ልማቱ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ በተደረገው ጥረት ወደ  ዘመናዊ አርብቶ አደርነት እየተሸጋጋሩ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ በአጭር ጊዜ ገቢ የሚያገኙበት ሁኔታ  ተፈጥሯል ብለዋል ።

አንዳን  ፀረ  ሰላም ኃይሎች ለአርብቶ አደሩ  ተቆርቋሪ  በመመስል የተለያዩ አፍራሽ  አሉባልታዎች በመንዛት  የልማት ሥራዎችን  ለማደናቀፍ  ሲሞክሩ መቆየታቸውን ጠቁሙው፤ የተገኙ ስኬታማ ውጤቶች አሉባልታዎች መሠረተ ቢስ እንዲሆኑ የበኩላቸውን ሚና መጫወታቸውን  አስገንዝበዋል ።

በመጨረሻም በተለያዩ የአርብቶ አደሩ ክልሎች በተለያዩ ዘርፎች  የተሻለ አፈጻጻም ያስመዘገቡ  390  አርብቶ አደሮች  ከጠቅላይ  ሚኒስትር ኃይለማርያም  አውቅናና ሽልማት  ተበርክቶላቸዋል ።

በጅግጅጋ ከተማ  በተካሄደው  16ኛው  የአርብቶ አደሮች ቀን በዓል  የኢጋድ አባል አገራት አርብቶ አደሮች ተወካዮች ፣ ከፍተኛ  የመንግሥት ባለሥልጣናትና ክቡራን እንግዶች ተገኝተዋል ።  

ቀጣይ 17ኛው የአርብቶ አደሮች ቀን በዓል በደቡብ ክልል እንዲከበር መወሰኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ፡፡