ሀገራዊ የውስጥ ችግሮች በራስ አቅም መፍትሄ አስቀምጦ መስራት በመቻሉ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተደማጭነት ማግኘት መቻሉን የፌደራል መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈትቤት ገለጸ ፡፡
የኢፌዴሪ መንግስት ከድህነት ለመውጣት የነደፋቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ማገዙን መንግስት ባወጣው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫው ጠቅሷል ፡፡
ይህም ሀገራዊ የውስጥ ችግሮችን መለየትና፡ በራስ አቅም ላይ የተመረኮዘ መፍትሄ አስቀምጦ መስራት በመቻሉም አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ተደማጭነት ጭምር ማግኘት መቻሉን ነው ያስገነዘበው ፡፡
በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ መድረክ ለማዘጋጀት ዕምነት የሚጣልበት አቅምም መፈጠሩንም እንዲሁ ፡፡
ሀገራችን በያዝነው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ 28ኛውን የአፍሪካ ህብረት መደበኛ ጉባዔ በማካሄድ ላይ እንደምትገኝ ነው መግለጫው የጠቀሰው ፡፡
በመዲናችን አዲስ አበባ የሚካሄደው አፍሪካ ህብረት መደበኛ ጉባዔም የአፍሪካ ሀገራ መሪዎች፣ የዓለምአቀፍ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮችና ከ4 ሺ በላይ እንግዶች የሚሳተፉበት መድረክ መሆኑን ገልጿል ፡፡
በዓለም ፈጣን የለውጥ ጉዞ ውስጥ የአፍሪካን የወደፊት ብሩህ ዕድል፡ በወጣቶቿ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚመክረውን ይህን ታሪካዊ ጉባዔ በስኬት ማጠናቀቅ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ አቅም ለመገንባቱ ማሳያ ነው ብሏል ፡፡
የኢትዮጲያ ህዝቦችና መንግስታቸው ትላንት ባደረጉት የጸረ ድህነት ትግል፡ ትላልቅ ሀገራዊና አህጉራዊ ሁነቶችን በተመሳሳይ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል አቅም መገንባቱን አረጋግጧል፡፡
ይህ አቅምም ከአህጉራዊና አለምአቀፋዊ መድረኮች ተጨማሪ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስችሎናል ሲል አስረድቷል ፡፡
ባለፈው ዓመት ተከስቶ የነበረው ድርቅ ህዝብና መንግስት በጋራ ርብርብ የተቋቋሙት ቢሆንም በዘንድሮም ዓመት በአርብቶ አደር አካባቢዎች በድጋሚ መከሰቱን አንስቷል ፡፡ ይሁን እንጂ መንግስት በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ፤ በጅግጅጋ ከተማ የተካሄደው የአርብቶ አደሮች ቀን ለዘላቂ መፍትሄ ለመስራት ምቹ ዕድል ፈጥሯል ብሏል ፡፡
ድርቅ በተከሰተባቸው የመንደር ማሰባሰብ፣ የእንስሳት መኖና የንፁህ መጠጥ ውሃ በማቅረብም በዘላቂነት ችግሩን ለመቋቋም ምርጥ ተሞክሮዎች የሚቀመሩበት መድረክ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡
በዚህ መልኩ በሀገር ውስጥ የሚፈጠር አቅም አርብቶ አደሩን ከሰላምና ከልማት እንዲጠቀምና ለሀገራዊ ህዳሴ ተጨማሪ አቅም እንዲሆን እንደሚያስችል አመልክቷል ፡፡
የኢፌዲሪ መንግስት ከአህጉራዊና አለምአቀፋዊ መድረኮች ተጨማሪ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማስፋት መስራቱን ይቀጥላል ነው ያለው ፡፡
የኢትዮጲያ ህዝቦችና የሚመለከታቸው አካላትም ዕንግዶችን በመቀበልና በኢትዮጲያዊ ጨዋነት በማስተናገድ ለሀገራዊ ገጽታ ግንባታ ስራ የበኩላቸውን እንዲወጡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡