አንቶኒዮ ጉተሬዝ የኢትዮጵያን ሠላምና ስደተኞችን የማስተናገድ ጥረት አደነቁ 

 

 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ሠላምና መረጋጋት በማስፈንና ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ረገድ የምታደርገውን ጥረት አደነቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በ28ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ከገቡት አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር በአሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ምክክር አካሂደዋል።

ዋና ጸሐፊው በዚሁ ጊዜ እንደገለጸት፤ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ሠላሟ የተጠበቀ አገር መሆኗ  በቀጠናው  ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን ተስፋ የሚሰጥ ነው።

በሶማሊያና ደቡብ ሱዳን እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች የአህጉሪቱ አካባቢዎች ሠላም ለማስፈን ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ጥረትም አወድሰዋል።

የሀገሪቱን ሰላም  ዋስትና አድርገው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡትን የጎረቤት አገራት ስደተኞች ተቀብላ በማስተናገድ ረገድም የምታደርገው  ሰብዓዊ ተግባር የሚመሰገን መሆኑንም ገልጸዋል።

ዋና ጸሃፊውም እነዚህንና ሌሎች ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው ተግባራት የመንግሥታቱ ድርጅት ድጋፍ እንደማይለያትም አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው በቀጣናውም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና ልማት እንዲረጋገጥ ከመንግሥታቱ ድርጅታ ጋር ኢትዮጵያ በቅርበት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

በኅብረቱ ጉባዔ አጀንዳዎችና ሌሎች አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያም በስፋት ምክክር ማካሄዳቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስተር ዴኤታ አቶ ዕውነቱ ብላታ ደበላ ገልጸዋል። 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በአዲስ አበባ በሚካሄደው 28ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የክብር ተጋባዥ ናቸው(ኢዜአ)።