መገናኛ ብዙሃን የመልካም አስተዳደር ማሳያ ሊሆኑ ይገባል – ጽህፈት ቤቱ

በአገር ውስጥ እየሠሩ የሚገኙ  የመገናኛ ብዙሃን የመልካም አስተዳደር ማሳያ ሞዴል  ሊሆኑ እንደሚገባቸው የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ዛዲግ አብርሃ ለመገናኛ ብዙሃን አመራሮች ፣ ጋዜጠኞችና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች  በተዘጋጀው የአምስት ቀን የመልካም አስተዳደር ላይ የተኮረ ሥልጠና ላይ እንደገለጹት የመገናኛ ብዙሃን በአገሪቱ  የመልካም አስተዳደር እንዲረጋጋጥ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ።  

የመገናኛ ብዙሃን ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን  ነቅሰው  ለማውጣት  የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በራሳቸው የመልካም አስተዳደርን  ማስፈን  እንደሚጠበቅባቸው አቶ ዛዲግ ተናግረዋል ።

በተለይም መገናኛ ብዙሃን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማጋለጥ  ህብረተሰቡን  በተገቢው መልክ ማወያያት ይገባቸዋል ያሉት አቶ ዛዲግ መገናኛ ብዙሃን መልካም አስተዳደር ላይ አስፈላጊውን ዘገባ በማቅረብ ተገቢውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ገልጸዋል ።

ሌላው የመገነኛብዙሃን በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች በወጡት ፖሊሲዎች ፣ አሠራሮችና ደንቦች አተገባባር ላይ  የሚታዩ  ክፍተቶችን በማሳየት ረገድም የመገናኛ ብዙሃን  የሚጠበቅባቸውን  ተግባራት ሊያከናውኑ እንደሚገባ አቶ ዛዲግ ጠቁመዋል ።

መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን  ውስጥ  የሚስተዋሉ የደሞዝ ማነስ ፣ የግብዓት እጥረቶች፣ የአቅምና ክህሎት ክፍተቶችን  ለመሙሏት  አስፈላጊውን  ድጋፍ  እንደሚያደርግም አቶ ዛዲግ አስረድተዋል ።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ  ስነ ምግባር የታነፀ በመሆን  በመረጃ  የተደገፈ የምርምራ  ጋዜጠኝነትን ሥራን  ተግባራዊ  ማድረግ እንደሚገባ ተመልክቷል ።

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ከመላ አገሪቱ ለተውጣጡ ከ200  ለሚበልጡ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች ፣ ጋዜጠኞችና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ያሳተፈ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሥልጠና  በዛሬው ዕለት ተጀምሯል ።