የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ አካባቢያቸው የተመለሱት የተሃድሶ ሥልጠና ተመራቂዎች ህዝባቸውን መካስ እንደሚጠበቅባቸው የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።
ጽህፈት ቤቱ በላከው ሳምንታዊ መግለጫ እንዳመለከተው ከትናንት በስተያ 11ሺ 352 የሚሆኑ የሁለተኛ ዙር የተሃድሶ ሠልጣኞች አስፈላጊው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ወስደው በመመረቃቸው ከህብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል ።
የሁለተኛ ዙር ሠልጣኞቹ በአራት ማዕከላት ለ20ቀናት በህገ መንግሥቱ፣ ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱ፣ አገሪቱ ስላለፈችበት ሂደትና የወደፊቱ አቅጣጫ ላይ የነበራቸውን ግንዛቤ የሚያሳድግ ሥልጠና ተሠጥቷል ።
በመጀመሪያው ዙር የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው የተመረቁት 9ሺ 800 ያህል ሠልጣኞች ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው ገንቢ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው የሁለተኛው ዙር ተመራቂዎችም ተመሳሳይ ገንቢ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል ብሏል ።
ሠልጣኞች ወደ መደበኛ ሥራዎቻቸውና ህይወታቸው በሚመለሱበት ጊዜ የሚመለካታቸው አካላት በሙሉ ተገቢውን ትብብር እንደሚያደርጉላቸው የጽህፈት ቤቱ መግለጫው አትቷል ።
ሠልጣኞች ወደ ህብረተሰቡ በሚቀላቀሉበት ወቅት ያገኙትን ሥልጠና ተጠቅመው በልማቱ ውስጥ የተሻለ ተሳትፎ በማድረግ ፤ ሌሎች የግንዛቤ እጥረት ያለባቸውን ማስተማርናማረም እንዳለባቸው በመግለጫው ተመልክቷል ።