መንግስት በርካታ ስኬቶች ቢኖሩትም ጎልቶ የሚነገረው ግን ስህተቶቹ ናቸው -ዶክተር ነገሪ ሌንጮ

የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ የሰላም፣የልማትና የዲሞክራሲ ስኬቶች ቢኖሩትም ጎልቶ የሚነገረው ግን ስህተቶቹ መሆናቸውን የኢፌዲሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አስገነዘቡ ፡፡

ሚኒስትሩ ይህንን ያስገነዘቡት፤በአዲስ አበባ ከተማ ለመገናኛ ብዙኋን፣ ለህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና አመራሮች ለአምስት ቀናት ሲሰጥ በቆየው ስልጠና ማጠቃለያ ላይ ትናንት ተግኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው ፡፡

መንግስት ባለፉት ዓመታት በሰላም፣በልማትና በዲሞክራሲ በርካታ ስኬቶች እንደተመዘገቡ ሁሉ በርካታ ስህተቶች መፈጸሙንም አንስተዋል ፡፡

በተለይም በአመራሩ ያለው ችግር እና በመልካም አስተዳደር የታዩ ጉድለቶች ዝርዝር በይፋ ለህዝብ ማሳወቁን ጠቅሰዋል ፡፡

መንግስት በተለይም በሙስናና በመልካም አስተዳደር የታዩት ስህተቶች መፍትሄ መስጠት እንጂ ችግሩ እንዲቀጥል መፍቀድ የለበትም ብለዋል  ፡፡

ዋናው ቁም ነገሩ መንግስት አመራር መለወጡ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ ፤መንግስት ዓላማውን ለማሳካት ምን መስራት እንደሚፈልግና የት መድረስ እንዳለበት ለህዝብ መግለጹን ነው ያመለከቱት ፡፡

ይሁንና በመገናኛ ብዙኋን የሚለቀቀው አሉታዊ ዘገባ ሲበዛ በመንግስት ላይ መተማመን እንደሚቀንስ ነው ያመለከቱት ፡፡

ስለዚህ ከአስር ዓመት በኋላ የሚመጣው አገር ተረካቢ ወጣት ምን ዓይነት አስተሳሰብ ሊይዝ እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል ፡፡

በዘረኝነት፣በሃይማኖት አክራሪነትና በሌሎችም ሴራዎች የተለወሰ የተዛባ አሉታዊ መረጃ ለወጣቱ መስጠት ወደ ተሳሳተ አስተሳሰብና ተግባር ሊያመራ ስለሚችል ዛሬ የሚታዩ አሉታዊ መረጃዎች መናቅ የለባቸውም ሲሉ ነው ያስገነዘቡት ፡፡

ለዚህም በሚኒስትር መሰሪያቤቱ በኩል የሚድያና ኮሚንኬሽን የአሰራር ለውጥ እየተጠበቀ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ደግሞ በዕውቀት የመሰረተ መረጃ መስጠና በቀበል እንዳለባቸው ነው ያስረዱት ፡፡

ትክክለኛ መረጃ በትክክል ለህብረተሰቡ መድረስ ስላለበትም መንግስት ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ ጠንካራ አስራር መዘረጋት ያስፈልጋል ብለዋል ፡፡

መገናኛ ብዙኋንና የህዝብ ግንኙነቱ መልካም የስራ ግንኙነት በመፍጠር ለኢትዮጵያ ህዝብ የተሻለ ኑሮ ለውጥ መትጋት እንደሚገባ ገልጸዋል ፡፡

መስሪያቤቱም ከሁሉም ሴክተር መስሪያቤቶችና ሚድያዎች ጋር ወርዶ አሰራሩን በቀጣይነት በመፈተሽ ለማስተካከል ጠንክሮ እንደሚሰራ ዶክተር ነገሪ አስታውቀዋል ፡፡