በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ባይፈጠር በቅድሚያ የሚጎዳው ህዝቡ መሆኑን የኢፌዲሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኢታ አቶ ዛዲግ አብረሃ ገለጹ ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ለአምስት ቀናት ሲካሄድ በነበረው የመገናኛ ብዙኋንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ስልጠና ላይ ጥናታቸውን ያቀረቡት አቶ ዛዲግ እንደገለጹት ፤በሰላም፣በልማትና በዲሞክራሲ ዙሪያ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ብሔራዊ መግባባት ላይ ደርሷል፡፡
ህዝቡ ህገ መንግሰቱን በማጽደቅና በመተግበር አብረታች ለውጦችን ማስመዘገቡን አስረድተዋል ፡፡
እስካሁን በተካሄዱት ምርጫዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ በነቂስ እየወጣ ያስተዳደረኛል ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጡ በሀገሪቱ ብሄራዊ መግባባት መስፈኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ህዝቡ ሰላሙን በመጠበቅ ረገድ እያደረገ ያለው ርብርብ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡
ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሯል ማለት ግን ሁከትና ብጥብጥ አይፈጠርም ማለት አይደለም ያሉት አቶ ዛዲግ ፤በቅርቡ በአገራችን አንዳንድ አከባቢዎች የተፈጠረው ሁከትም የዚሁ ነጸብራቅ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡
ህዝብ መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነትን፣ ብልሹ አሰራርንና ሙስናን ያስወግድልን ፤ መልካም አስተዳደር ያረጋግጥልን በሚል የተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥያቄው በወቅቱና ባግባቡ ካልተመለሰ አደጋው የከፋ መሆኑን አቶ ዛዲግ አስገንዝበዋል፡፡