ጠ/ሚ ኃይለማርያም ለአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የ“እንኳን ደስ አለዎት” መልዕክት አስተላለፉ

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ  ለአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ “እንኳን ደስ አለዎት” በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገለጹ።

የቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ምርጫው እንዲሳካ ለሰጡት ቁርጠኛ አመራር ያላቸውን አድናቆትም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከሶማሊያ መንግስትና ህዝብ እንዲሁም ከተመራጩ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ጋር እንደምትሰራም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል። የሁለትዮሽ ግንኙነቷንም አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ፕሬዚዳንቱ የስራ ዘመናቸው የተሳካ እንዲሆን በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ስም መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ በአገራቸው ለተካሄደው ምርጫ ስኬታማነት ለሰጡት ቁርጠኛ አመራር ምስጋናና አክብሮታቸውን ገልጸው፣ ይህም በሶማሊያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እየተጠናከረ መምጣቱን እንደሚያመለክት ነው ያስታወቁት።

የአገሪቱ ፓርላማ የላይኛውና የታችኛው ምክር ቤት አባላት ምርጫ ከሶስት ወራት በፊት መከናወኑ ይታወሳል-( ኢዜአ)