በአጠቃላይ በመላ አገሪቱ በሲቪል ሰርቪስ ዘርፍ ለወራት ሲካሄድ የቆየው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ውጤታማና ግቡን የመታ እንደነበር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃይል ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ ።
በሚኒስቴሩ የኮሚኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አብዲሳ ለዋልታ እንደገለጹት በመላ አገሪቱ በሲቪል ሰርቪሱ ዘርፍ ሲካሄድ የቆየው የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ የዘርፉን ጥንካሬና ድክመት ለመለየት የተቻለበት ነው ብለዋል ።
የተሃድሶ ንቅናቄው በመላ አገሪቱ የሚገኙትን 1ነጥብ4 ሚሊዮን ሠራተኞችን ባሳተፈ ሁኔታ መካሄዱን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው ከፌደራል ደረጃ ፣ክልሎችና የወረዳ አስተዳደሮች ድረስ ሠራተኛው ተሳታፊ እንዲሆን ተደርጓል ።
በተሃድሶ ውይይት ወቅት ሠራተኛው በግልጽነት በሲቪል ሰርቪሱ ዘርፍና በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች እየታዩ ስላሉት ችግሮችና ጥንካሬዎች በማንሳት ጠቃሚ ውጤት ተገኝቶበታል ።
በሲቪል ሰርቪሱ የተሃድሶ ንቅናቄ በአገልግሎት አሠጣጥ ረገድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየትና መልካም ተሞክሮዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በሚያስችል ሁኔታ ሁሉም ሠራተኛ ወደ ራሱን በመውሰድ ጠንካራ ግምገማ ማድረጉን አቶ ጌታቸው አስረድተዋል ።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ በጥልቅ ተሃድሶው ውይይት ወቅት በተሳታፊዎች የተነሱት የኪራይ ሰብሳቢነት ፣ የአመለካከትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችንናክፍተቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚመለከታቸው ተቋማት እርምጃዎች እንዲወስዱ ይደረጋል ።
በመጨረሻም ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በተለያዩ ዘርፎች በሚካሄዱት የተሃድሶው ነቅናቄ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት ለሥር ነቀል ለውጥ እንዲሠሩ አቶ ጌታቸው ጥሪ አቅርበዋል ።