ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር እየሰሩ ነው

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጄምስ ፒታ ሞርጋን ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር ጥረቱ በተለያዩ ዘርፎች ቀጥሏል፡፡

እንደ አምባሳደሩ ማብራሪያ ሁለቱ አገሮች በንግድ፣ መንገድ፣ ባቡር፣ የነዳጅ መስመር፣ ኃይል፣ ሰላምና መረጋጋት ዘርፎች ይበልጥ ተቀራርበው መስራት የሚያስችላቸውን የውል ስምምነት በቅርቡ ለመፈራራም ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

በቅርቡ በአንዳንድ ማሕበራዊ ሚዲያዎች በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ ነው የሚለው፣ መረጃ ከሐሰት የራቀ እንደሆነና በተለይም መረጃው ከደቡብ ሱዳን አማፂዎች የሚነዛ ልብ ወለድ ፕሮፓጋንዳ እንጂ ምንም መሰረት የለውም ሲሉ አምባሳደሩ አክለው ገልጸዋል፡፡

በተሳሳይ ሁኔታም የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት በ24 ሰዓታት ውስጥ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ከኢትዮጵያ መንግስት መመሪያ ተላልፎባቸዋል የሚለው ሐሳብም ከሐቅ የራቀ ነው፡፡ “እኔ በኢትዮጵያ የቤቴ ያህል ይሰማኛል፤ በቀጣይ ለማከናወን ያቀድናቸውን ፕሮጄክቶች በተግባር መግለጽ ከቻልን አሉባልታዎች ሁሉ በራሳቸው ጊዜ እየከሰሙ ይሄዳሉ፡፡” ሲሉ አምባሳደር ሞርጋን ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን ሳልቫኪርና ሪክ ማቻር ቀደም ሲል ሰላምና መረጋጋት በሀገሪቱ ለማስፈን የሰላም ስምምነት ፊርማቸውን ካኖሩ በኋላ በተግባር የታገዘ እንቅስቃሴ እየሰደረጉ ባይሆንም አሁን ላይ በአብዛኞቹ የደቡብ ሱዳን ክፍሎች የተሻለ ሰላምና መረጋጋት እንደሰፈነ ታውቋል፡፡

ቀደም ሲል በደቡብ ሱዳን የሙርሌ የታጣቂዎች ቡድን ከጋምቤላ ክልል ከተወሰዱት ሕጻናት 94ቱ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው እንደተቀላቀሉና በቀጣይም በአካባቢው ያለውን የድንበር ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት በሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየተሰራ እንደሆነም አምባሳደሩ ጠቁመዋል፡፡

ደቡብ ሱዳን ነፃ ሀገር በመሆን ራሷን የቻለችው በሐምሌ 2003 ዓ.ም. እንደነበር ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡