የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ / ህወሃት/ 42ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በዛሬው እለትበመቀሌ የሰማዕታት ሐውልት እየተከበረ ነው።
የህወሃትን 42ኛ ዓመት ምስረታን አስመለክቶ የደርጅቱ ማእከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ፥ የዘንድሮው በአል የተጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞን በማጠናከር ሀገራዊ አንድነታችንን እና ልማታችንን ለማፋጠን ለህዝባችን ቃል የምንገባበት ነው ብሏል ።
ህወሃት በገጠር ግብርና መር የሆነው ፖሊሲ የክልሉን አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥም ባለፈ ጥሪት እንዲቋጥሩ እያስቻለ ነው ብሏል ።
በከተሞችም በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በጥቃቅን እና አነስተኛ የሥራ ዘርፎች ተደራጅተው ሃብት ማፍራት መጀመራቸውን ነው መግለጫው ያመላከተው፡፡
ይሀን እንጂ ከእድገቱ ጋር ተያይዞ እና በተለያዩ ምክንያቶች እየታዩ ያሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታት፥ ከህዝቡ ጋር በድርጀቱ ጥላ ስር በመሰባሰብ ችግሮቹን አንድ በአንድ ለመፍታት ቃል የምንገባበት ቀንም ነው ብሏል።
የህወሃት 42ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በአባላቱ እና በሀገሪቱ የትግሉ አጋር እየተከበረ ሲሆን፥ በመቀሌ የሰማዕታት ሐውልትም አየተከበረ ነው፡፡
በስፍራው የህወሃት ሊቀመንበር እና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ፣ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳድር፣ የአማራ ክልል መንግስት ተወካዮች፣ የሱዳን የተለያዩ ግዛቶች በተለይ የገዳሪፍ፣ የከሰላ፣ የብሉናይል እና የሲናር ግዛት መሪዎችም የተገኙ ሲሆን በሰማዕታት ሐውልት ስር የአበባ ጉንጉንም አኑረዋል፡፡
የህወሃት ፅህፈት ቤት የሰማዕታት ቤተሰብ፣ የጦር አካል ጉዳተኞች ማህበር እና ሌሎችም ጉንጉን አበባ አኑረዋል፡፡
በዓሉ በዛሬው እለት በሁሉም የክልሉ ከተሞች እየተከበረ ይውላል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)