ከአውሮፓና ከእስያ ሃገራት ግዙፍና ታዋቂ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ መግባታቸውን የፌደራል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አስታወቀ ፡፡
ጽሕፈትቤቱ ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫው እንዳመለከተው፤ ከዘመናዊ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ጋር በተያያዘ ባለፉት ስድስት ወራት ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከእስያ ሃገራት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ሶስት የቻይና፣ ሁለት የህንድና የሌሎች አገራት ኩባንያዎች በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተዋል ፡፡
አንድ የውጭ ባለሃብት ወደ አንዲት አገር ተንቀሳቅሶ በዚያች አገር መዋዕለ ንዋዩን ከማፍሰሱ በፊት በዓለም ላይ ያሉትን አገራት ሁሉ ያነጻጽራል ብሏል መግለጫው ፡፡
የውጭ ባለሃብቱ በየአገሮቹ የቀረቡለትንም አማራጮች በሙሉ ይፈትሻል፤ ያወዳድራል፤ በመረጣት አገር ውስጥ በእርግጥም መዋዕለ ንዋዩን ቢያፈስ ከሌሎቹ አገሮች ሁሉ በተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆን ሳያረጋግጥ ወደተግባር እንደማይገባ የተረጋጠ መሆኑን አብራርቷል ።
ከዚህ አንጻር አገራችን የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የእስያ ግዙፍና ታዋቂ ኩባንያዎችን ቀልብ ለመማረክ የቻለችው በእርግጥም ለኢንቨስትመንት የተሻለ ተመራጭ ሆና በማግኘትዋ ነው ያለው ።
ይህም በዋነኝነት በመላ አገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እና መረጋጋት በመኖሩ መሆኑን አስረድቷል ። ባለሃብቶቹ ለንብረቶቻቸውም ዋስትና የተረጋገጠባት አገር መሆኗን ጠንቅቀው በማወቃቸው መሆኑንም እንዲሁ ።
የውጭ በለሃብቶቹ በፍጥነት እያደገ ያለ መሠረተ ልማትን አገሪቱ እያቀረበች መሆኗንም በማመናቸው መሆኑን ነው መግለጫው ጨምሮ ያመለከተው ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እየወጡ ያሉ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት አገራችን ኢትዮጵያ የኢንቨስተሮችን ትኩረት እየሳበች ትገኛለች ብሏል ።
ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሚወጡት መረጃዎች በበኩላቸው እንደሚጠቁሙት በስድስት ወራት ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የተመዘገበው ካፒታል መጠን 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መሆኑን ገልጿል ።
ይህ አፈፃፀም በ2008 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት እና በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ከተመዘገበው አማካይ አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር በ35 በመቶ ብልጫ አለው ብሏል ፡፡
ከየክልሎቹ የሚወጡት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የአገር ውስጥ ባለሃብቶችም በኢንቨስትመንት ተግባር ላይ በስፋት እየተሳተፉ መሆናቸውን እንደሚያመልክት ጠቁሟል ።
ይህ ውጤት ደግሞ ህዝብና መንግሥት ለዓመታት ያደረጉት የልፋት ውጤት መሆኑን ነው ያስገነዘበው ።
በመሆኑም “በተያያዝነው የተሃድሶ እንቅስቃሴ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለዘለቄታው በመፍታት የኢንዱስትሪ ልማታችን ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር ለሆኑት የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች የተሻለ የኢንቨስትመንት አማራጭ መሆናችንን እንቀጥላለን! ብሏል” መግለጫው ።