የህወሓት ታጋዮችን መስዋዕትነት የአገሪቷን ህዳሴ በማረጋገጥ መመለስ ይገባል

የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ /ህወሓት/ ታጋዮች የከፈሉትን መስዋዕትነት የአገሪቷን ህዳሴ ለማረጋገጥ በመረባረብ መመለስ እንደሚገባ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አስገነዘቡ ።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሠራተኞች 42ኛውን የህወሓት ኢህአዴግ ምስረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።

የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አራቱን ብሄራዊ ድርጅቶች ወክለው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የህወሓት የትጥቅ ትግል የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የነጻነት፣ የእኩልነት፣ የፍትህና የማንነት ማረጋገጫ እሴትና ትሩፋት የተረጋገጠበት መሆኑንም በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።

"42 ሲቆጠር ቁጥር ነው፤ ነገር ግን በደም የተገነባ ትልቅ እሴት ያረጋገጡ፤ ፍትህ ዴሞክራሲና ሠላም የህዝቦች እሴት እንዲሆኑ ያደረጉ ውድ የመስዋዕትነት ውጤት ዓመታት ናቸው" ብለዋል።

ትግሉ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት በማስወገድ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት የተረጋገጠበት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሽፈራው ለተገኘው ድል የትግራይ ህዝብና ህወሓት ውድ ዋጋ መክፈላቸውን አስገንዝበዋል።

"የቀደሙት ታጋዮች ህዳሴዋ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመፍጠር መስዋዕት ሆነዋል" ያሉት አቶ ሽፈራው ታጋዮቹ የወደቁለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ዋነኛ ጠላት ድህነት መሆኑን በመጥቀስም ድህነትን ለማስወገድ ከህወሓት የትግል ታሪክ በጽናት መታገልን መማር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

የብአዴን ተወካይ አቶ እሸቴ አስፋው በሰጡት አስተያየት ህዝቡ ከህወሓት የትግል ታሪክ ጽናትን፣ አንድነትንና ይቻላል ባይነትን መማር ይኖርበታል ብለዋል።

"ብአዴንና ህወሓት በደምና በአጥንት የተገነቡ፣ አንድ ዋጋ የከፈሉ ናቸው" ያሉት ተወካዩ ብአዴን ለኢትዮጵያ ህዳሴ ስኬት ከህወሓት ጋር ተባብሮ መስራቱን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ከህወሓት ኢህአዴግ የመጡት አቶ ይርጋለም መዓሾ በበኩላቸው የቀደሙት ታጋዮች የከፈሉት መስዋዕትነት አሁን ላለው ሠላም፣ ዕድገትና ዴሞክራሲ መሰረት መጣሉን ገልጸዋል።

ተተኪው ትውልድ የታጋዮችን አደራ በመረከብ ድህነትን ለማጥፋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ማጠናከር አለበት ብለዋል።

"አሁን የትጥቅ ትግል ጊዜ አልፏል፤ ጊዜው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የአስተሳሰብ ትግል የሚደረግበት ነው" ሲሉም አስታውቀዋል።

የኪራይ ሰብሳቢት አመለካከትን መመከት የሚያስችል የአስተሳሰብ ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልግም አክለዋል።

በበዓሉ ላይ ለታጋይ ሰማዕታት የህሊና ጸሎትና የጧፍ ማብራት ስነ-ስርዓት የተካሄደ ሲሆን በዓሉን በአስመልክቶ ከህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የወጣ መግለጫም በንባብ ቀርቧል-(ኢዜአ)፡፡